በጤና ተቋማት በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ

በጤና ተቋማት በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ

በጤና ተቋማት በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

ቢሮው የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ጥምረት ለጥራት መድረክ በዲላ ከተማ አካሂዷል፡፡

መድረኩን የመሩት የደቡብ አትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትልና የህክምና አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ እንደገለጹት፤ በጤና ተቋማት በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በተቋማቱ የሚከናወኑ ተግባራትን በየጊዜው በመገምገም በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ እንደ ሀገር በተጀመረው “የጤና ክብካቤ ጥምረት ለጥራት” በመጀመሪያ ዙር የሪፎርም ሥራዎችን እየሠሩ መቆየታቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፤ አፈፃፀሙን በመገምገም የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ጤና ተቋማት በክልልና በፌዴራል መንግሥት ዕውቅና መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡

በመጀመሪያ ዙር “የጤና ክብካቤ ጥምረት ለጥራት” በተከናወኑት ተግባራት የታዩ ክፍቶችን ለይቶ በማረም በቀጣይ ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ፕሮግራም በ2ኛ ዙር መጀመሩን አቶ ናፍቆት በማስታወቅ በዚህም በህክምና አገልግሎት ዘርፍ ማህበረሰቡ የሚያነሳቸዉን ጥያቄዎች ለመመለስና ጥራት ያለዉን የጤና አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ለማዳረስ የጤና ተቋማት ጥምረት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

የጤና አገልግሎቱን በጥራት ለመስጠት እንደ ሀገር በተቀመጠው አቅጣጫ የሚከናወኑ ተግባራትን በመገምገም ከባለድርሻ አካላት በጥምረት በመሥራታቸው በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የጤና ተቋማትን ማፍራት መቻላቸውን ከውይይቱ ተሳታፊዎች የጌዴኦና ወላይታ ዞን ጤና መምሪያ የህክምና አገልግሎቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይ ዘውዴ እና እንድሪያስ ኤልያስ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን