የትምህርት ውጤት ስብራትን ለመጠገን በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለፀ

የትምህርት ውጤት ስብራትን ለመጠገን በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለፀ

መምሪያው የ2017 ዓ.ም የምዘና፣ የቲቶሪያል ኦረንቴሽንና ወቅታዊ ስራዎች በተመለከተ የምክክር መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን የትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም እንደገለፁት፤ እንደሀገር እንዲሁም እንደዞን ያጋጠመውን የትምህርት ውጤት ስብራት ለመጠገን ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት ይገባቸዋል።

ከዚህ በፊት በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ መምህራን ይሰጥ የነበረው የቲቶሪያል ትምህርት በዞኑ የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ እንደነበረው ያነሱት አቶ መብራቴ፤ በተያዘው የትምህርት ዘመን የከዚህ ቀደሙን ልምድ በመጠቀም የተጠናከረ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለተማሪዎች የቲቶሪያል ትምህርቱን በተገቢው ለመስጠት የትምህርት አመራሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዳለበት ገልጸዋል ሀላፊው።

ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪ ለማፍራት በየደረጃ የሚገኙ መምህራን በያዙት የትምህርት አይነት ተገቢውን ስራ መስራት እንደሚጠበቅባችው አስታውቀዋል አቶ መብራቴ።

የመምህራን የምዘና ውጤት መውደቅ የሚያመላክተው የቅድመ ዝግጅት ስራ አለማድረግ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ በቀጣይ ምዝገባ በማካሄድ በተመረቁበት የትምህርት ዓይነት በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ጥሩነሽ ምኑታ በበኩላቸው፤ መምህራን ምዘናውን በተገቢው እንዲወስዱ የተጠናከር ስራ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በተለይም የመምህራን እጥረት ባለባቸው የትምህርት አይነቶች ላይ በልዩነት የማካካሻ ትምህርት መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል ወ/ሮ ጥሩነሽ።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በትምህርት ጥራት ላይ የተፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ የሚቻለው ከመምህራኖች ተግባቦት በመፍጠር የብቃት ማረጋገጫ ምዘና መስጠት ሲቻል ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

የመምህራንን አቅም ለማሳደግ ምዘናውን በተገቢው እንዲወስዱ መስራት ይገባል ሲሉም አክለዋል።

የመጽሀፍ አሰባሰብ ላይ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው መዋቅሮች በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ እርካብነሽ ወ/ማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን