በምዕራብ ኦሞ ዞን በባቹማ ከተማ አስተዳደር በከብት እርባታ እና በዶሮ እርባታ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናገሩ
በከተማው የሌማት ትሩፋትን በስፋት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
በምዕብ ኦሞ ዞን ባቹማ ከተማ አስተዳደር 02 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ መሠረት ባደግ በከተማው ያለውን የወተት እጥረት በማየት በከብት እርባታ ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆን በዚህም የገቢ አቅማቸውን ከማሳደግ ባለፈ የቤተሰባቸውን የወተት ፍላጐት በበቂ ሁኔታ መመለስ ችለዋል፡፡
ከሁለቱ ከብቶች በቀን ከ40 ሊትር በላይ ወተት በማምረት በወር እስከ 80 ሺህ ብር ገቢ እያገኘን ነው የሚሉት አቶ መሰረት፤ ስራውን ይበልጥ ለማስፋፋት የቦታ እጥረት ፈተና እንደሆነባቸው ጠቁመው ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ሌላኛው በከተማ አስተዳደሩ የዱልኩባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት መምህር ያለው ባዩ ከ2014 ጀምሮ በዶሮ እርባታ የስራ ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚነታቸው እያሳደጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ስራውን ሲጀምሩ በ500 የ1 ቀን ጫጩቶች ማርባት ሲሆን ባለፉት 3 ዓመታት ጠንክረው በመስራታቸው አሁን ላይ ከ2 ሺህ በላይ የ1 ቀን ጫጩቶችን ከማርባት ባለፈ የእንቁላል ጣይና የስጋ ዶሮ ወደ ማርባት መሸጋገር መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
መምህር ያለው ስራውን ይበልጥ ለማስፋፋት የቦታ እጥረት ትልቁ ፈተና እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡
የባቹማ ከተማ አስተዳደር ኢንተኘራይዝ፣ ትራንስፖርትና ግብርና ክላስተር አስተባባሪ አቶ ግርማ ጊሚ እንደተናገሩት፤ በከተማው በሚገኙ 5 ቀበሌዎች ላይ የተለያዩ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን በትኩረት እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በከተማው በዶሮ እርባታ፣ በከብት እርባታና በንብ ማነብ ስራዎች ማህበረሰቡ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ የድጋፍና ክትትል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የባህል ስፖርቶችና የባህል ፌስቲቫል ውድድር ቱባ የሆኑ ባህላዊ ስፖርቶች ጎልተው የታዩበት ሠላምና አንድነት የተጠናከረበት ውድድር መሆኑን ቢሮው አስታወቀ
በማህበር በማደራጀት ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ገለፀ
በልማቱ ዘርፍ የመጣው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው አንድነትን በማጠናከር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር አሳሰበ