ማህበራዊ ችግሮችና የዜጎች ተጋላጭነትን በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን ቀርፆ እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ
ሀዋሳ፣ የካቲት 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ማህበራዊ ችግሮችና የዜጎች ተጋላጭነት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ መንግስት እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን ቀርፆ የማህበራዊ ጥበቃ ሥራ እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የ2017 ዓ.ም የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ሥራ ፕሮግራም መሠረታዊ ማህበር አገልግሎት ትስስር ዙሪያ ለክልል፣ ዞንና ወረዳዎች ቴክኒክ ቡድን ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ስልጠና በጂንካ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዋኖ ዋሎሌ እንደገለጹት፤ ከማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ትኩረት ጉዳዮች ውስጥ ልማታዊ ሴፍትኔት አንዱ ሲሆን የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ናቸው፡፡
ፕሮግራሙ ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ፍላጎችን ለማሟላት የአጭር ጊዜ የምግብ አቅርቦት ችግርን በማቃለል ዜጎችን በቀጣይ ከከፋ ድህነትና ከተመጣጠነ የምግብ እጦት ችግር በራሳቸው ጥረት ደረጃ በደረጃ በማላቀቅ ዘላቂነት ባለው መልኩ እንዲቋቋሙና የተሻለ ኑሮን እንዲመሩ የተመቻቸ ሁኔታን የሚፈጥር ስትራቴጂ ነው ብለዋል ዶ/ር ዋኖ።
ሥራውን ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በአግባቡ መርተው ግቡ እንዲሳካ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ዶ/ር ዋኖ ዋሎሌ አሳስበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በልማታዊ ሴፍትኔት ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችና ሌሎች አካላት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰው የተሰጣቸው ተጨማሪ ግንዛቤ ይበልጥ በዘርፉ ጠንክረው እንዲሠሩ አቅም ያገኙበት መድረክ እንደነበር ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የባህል ስፖርቶችና የባህል ፌስቲቫል ውድድር ቱባ የሆኑ ባህላዊ ስፖርቶች ጎልተው የታዩበት ሠላምና አንድነት የተጠናከረበት ውድድር መሆኑን ቢሮው አስታወቀ
በማህበር በማደራጀት ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ገለፀ
በልማቱ ዘርፍ የመጣው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው አንድነትን በማጠናከር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር አሳሰበ