የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባላት የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚሠራ የኮሬ ዞን አስተዳደር ገለጸ
የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ በወቅታዊ ዞናዊ ተግባራት ላይ ከደሬቴድ ይርጋጨፌ ቅርንጫፍ ሬዲዮ ጣቢያ ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባላት የመታወቂያ ዕድሳት ስራ በዞኑ እየተሠራ ነው።
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት በዞኑ ከተጀመረ ወዲህ በአነስተኛ ዓመታዊ መዋጮ አባል በመሆን በየደረጃው ባሉ ጤና ተቋማት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
በዞኑ አገልግልቱ በይፋ ከተጀመረ ወዲህ በርካቶች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ያሉት አስተዳዳሪው ከ3.6 ሚሊየን ብር በላይ በተለያዩ የጤና ተቋማት ለተሰጡ አገልግሎቶች መከፈሉን አብራርተዋል።
አሁን ላይ የአባላት መታወቂያ ዕድሳት ተግባሩ በይፋ ተጀመሮ እየተሰራ ያለ ሲሆን እስከ የካቲት 30/2017 ዓ.ም የሚቆይ ቢሆንም ከታቀደው ዕቅድ አንጻር አፈጻጸሙ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሆነና ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
በሚያዋጡት ገንዘብ መጠን በከፍተኛ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ደረጃ የሚመደቡ አባላትን በመለየቱ በኩል በትኩረት እንዲሰራ ያሳሰቡት አስተዳዳሪው፤ ሁሉም አባላት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ በመፈጸም የታደሰውን መታወቂያ እንዲይዙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባላት የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት መደብር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመክፈት አቅጣጫ ስለመቀመጡም ነው የገለጹት።
በተጨማሪም ለማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባላት የአንድ መስኮት አገልግልት ያለመጀመሩ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለ በመሆኑ በሚስተካከልበት ዙሪያ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች የሚሰሩ ተግባራት መጠናከር እንዳለባቸውና ህብረተሰቡም የጤና መድን አገልግሎት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
በዞኑ ከ42 ሺህ በላይ አባወራ እና እማወራዎች አባል ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን 24 በመቶ የሚሆኑት በመንግስት ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑን የዞኑ ጤና ዩኒት መረጃ ያሳያል።
ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የባህል ስፖርቶችና የባህል ፌስቲቫል ውድድር ቱባ የሆኑ ባህላዊ ስፖርቶች ጎልተው የታዩበት ሠላምና አንድነት የተጠናከረበት ውድድር መሆኑን ቢሮው አስታወቀ
በማህበር በማደራጀት ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ገለፀ
በልማቱ ዘርፍ የመጣው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው አንድነትን በማጠናከር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር አሳሰበ