በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት በዘመቻ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት በዘመቻ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ

ክትባቱም እድሜያቸዉ ከ5 አመትና ከዚያ በታች ለሆኑ ህፃናት ከየካቲት14 – 17/2017 ዓ.ም ለተከታታይ አራት ቀናት የመጀመሪያ ዙር የፖሊዮ ክትባት እንደሚሰጥ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነብዩ ቤዛ ተናግረዋል።

በክትባት ዘመቻዉም ከ1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህፃናትን የፖሊዮ ክትባት ለመስጠት ግብ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ተጠቁሟል።

በክትባት ትግበራ ችግር ምክንያት አንድም ህፃን በፖሊዮ በሽታ እንዳይጠቃ ትኩረት ተሰጥቶ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንና የገለጹት ም/ኃላፊው ለዚህም ህፃናት መከተብ መብታቸዉ ሲሆን ወላጆች የማስከተብ ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል።

የፖሊዮ ክትባት ከዚህ ቀደም የተከተቡም ያልተከተቡም ህጻናት የሚወስዱ በመሆኑ ወላጆች ሀላፊነታቸዉ መወጣት እንደሚገባቸው የደቡብ ኢትዮጱያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ዳይሬክተር እና የክትባት ዘመቻው አስተባባሪ አቶ አስራት በሻ ተናግረዋል፡፡

ክትባቱ የመጀመሪያ ዙር ከተሰጠ ከአንድ ወር በኋላ ቀጣይ የሚሰጥ ሲሆን ክትባቱም ቤት ለቤት በመዘዋወር የሚሰጥ መሆኑንና ለዚህም አስፈላጊዉ ግበአት 96 በመቶ ወደየአከባቢዉ መሰራጨቱን ተጠቁሟል፡፡

ይህንን በሽታ ለመከላከል የሀይማኖት አባቶች ፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሚዲያ ባለሞያዎችና ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የድርሻዉን ሊወጣ ይገባል ሲል ቢሮው ጥሪ አቅርቧል፡፡

ዘጋቢ፡ መሳይ በዛብህ – ከጂንካ ጣቢያችን