ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በ14ኛው ዙር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 343 ተማሪዎችን አስመርቋል

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በ14ኛው ዙር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 343 ተማሪዎችን አስመርቋል

መንግስት በትምህርት ዘርፍ የነበሩ ስብራቶችን ለመጠገን ባከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል ባስተላለፉት መልዕክት፤ መንግስት በትምህርት ዘርፍ የነበሩ ስብራቶችን ለመጠገን ባከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በዩኒቨርስቲው ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።

ዩኒቨርስቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በማህበረሰብ ተኮር ዘርፍ ላይ የሚሰጠውን አገልግሎት በብዛትና በጥራት እያሳደገ የመጣ ዩኒቨርስቲ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።

ሀገሪቱ በፈተናዎች ውስጥ እየተሻገረች የተለያዩ አስደናቂ ውጤቶችን እያስመዘገበች መሆኑን ያነሱት ዶክተር ፋሪስ፤ ተመራቂዎች ሀገሪቱ በምትፈልጋቸው ቦታዎች ብርቱ አገልጋዮች እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የዩኒቨርስቲው ሬጅስትራር ዳይሬክተር ዶክተር ዮናታን ሙሉሸዋ፤ ተመራቂዎች ብዙ የትምህርትና የህይወት ፈተናዎችን በትጋትና በጽናት በማለፍ ለዚህ መብቃታቸው አንስተዋል።

በመደበኛ መርሃግብር በመጀመሪያ ዲግሪ በህክምናና ጤና ሳይንሰ እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛ፣ በክረምትና በተከታታይ ትምህርት በተለያዩ የትምህርት መስኮች 343 ተማሪዎች መመረቃቸውን ዶክተር ዮናታን ገልጸዋል።

በዩኒቨርስቲው ቆይታቸው ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ እዚህ ደረጃ በመድረሳቸው መደሰታቸውን ተመራቂ ተማሪዎች ተናግረዋል።

በተማሩበት የሙያ መስክ ያስተማራቸውን የህብረተሰብ ክፍል በትጋት እንደሚያገለግሉ ያነሱት ተመራቂዎቹ በቀጣይም ጠንክረው በመማር ውጤታማ ለመሆን እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ዳዊት ዳበራ – ከወልቂጤ ጣቢያችን