የበጋ መስኖ ልማት ከጀመሩ ወዲህ ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ መምጣቱን በሀላባ ዞን ዌራ ወረዳ አንዳንድ አርሶአደሮች ተናገሩ

የበጋ መስኖ ልማት ከጀመሩ ወዲህ ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ መምጣቱን በሀላባ ዞን ዌራ ወረዳ አንዳንድ አርሶአደሮች ተናገሩ

የወረዳው ግብርና ልማት ጽ/ቤት በበኩሉ በበጋ መስኖ ልማት 80 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ እና የተለያዩ ሰብሎችን ለማልማት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በወረዳው ያነጋገርናቸው አንዳንድ አርሶ-አደሮች እንዳሉት በበጋ መስኖ በቆሎ እና የተለያዩ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ እያለሙ ለቤት ፍጆታ ከመጠቀም አልፈው ለገበያው እያቀረቡ ገበያውን በማረጋጋትና ተጠቃሚነታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደጉ ነው።

በወረዳው የታችኛው በደኔ ቀበሌ ልማት ባለሙያዋ ወይዘሮ ዘሐራ አብዱልሃዲ፤ አርሶአደሮች ለበጋ መስኖ ልማት ትኩረት ሰጥተው በመስራት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ አልፈው ያለሙትን ሰብሎች ወደ ገበያ አቅርበው ገበያው እንዲረጋጋ ለማድረግ ለስራው ትኩረት እንዲያደርጉ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸዉን ተናግራለች።

በሀላባ ዞን የዌራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል ሚሃሌ፤ በዘንድሮው በበጋ መስኖ ልማት በወረዳው በ6 ቀበሌዎች 81 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎና የተለያዩ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት ከታቀደው እስከአሁን ባለው ሂደት 99 በመቶ በዘር መሸፈኑን ገልፀዋል።

መንግስት ለበጋ መስኖ ልማት ትኩረት በሰጠው መሠረት በወረዳው የሚገኙ አርሶአደሮች በአካባቢያቸው ያለውን የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በበጋ መስኖ በቆሎ፣ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን እና የተለያዩ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እያለሙ ለቤት ፍጆታ ከመጠቀም ባሻገር ለቁሊቶ ከተማ ማህበረሰብ እያቀረቡ ገበያውን በማረጋጋት ረጋድ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን አቶ ጀማል ሚሃሌ ተናግረዋል።

የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪው አክለውም በወረዳው የሚገኙ አርሶአደሮች በአካባቢያቸው ያለውን የውሃ አማራጭ ተጠቅመው ለበጋ መስኖ ልማት ትኩረት እንዲሰጡ ለግብርና ባለሙያዎች እና ለአርሶአደሮች ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ለስራ አሰፈላጊ የሚሆኑ ግብዓትን በማቅረብ በርካታ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ አርሶአደሮች በመስኖ ያለሙትን የተለያዩ ሰብሎችን ወደ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ከዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ጋር በመቀናጀት የገበያ ትስስር በመፍጠር የተለየዩ ስራዎች እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ሙዘይን ሳኒ – ከሆሳዕና ጣቢያችን