ወቅቱ በጋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሰደድ እሳት ስጋት በመኖሩ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኮሬ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ዩኒት አሳሰበ

የኮሬ ዞን በደን የተሸፈኑ ሰንሰለታማ ተራሮች ያሉት ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች እየወደመ ይገኛል።

አቶ ዘብዴዎስ ሽብሩ በኮሬ ዞን የደን እና አካባቢ ጥበቃ ዩኒት የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቡድን መሪ እና የጽ/ቤቱ ተወካይ እንደተናገሩት፣ ጽ/ቤቱ በደን ልማት፣ በብዝሃ ሕይወት እና አካባቢ ጥበቃ ላይ በትኩረት ይሠራል።

በዞኑ በተፈጥሮ ያሉ ደኖች ተከልለው እንዲጠበቁ በተሠራው ሥራ ዘንድሮ አምስት የሚሆኑ የደን ሥፍራዎችን ማካለል መቻሉንና ይህም በህገ-ወጥ መንገድ ደንን በሚወሩ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ አጋዥ መሆኑን አመላክተዋል።

ሌሎች የደን ሥፍራዎችን ለማካለል እየተሠራ ነው የሚሉት አቶ ዘብዴዎስ፣ ህግን ለማሥከበር እየተሠራ ባለው ሥራ ከ3 መቶ 50 በላይ ህገ-ወጦችን እርምጃ ለማስወሰድ በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ያለ ደን የሰው ልጆችን ጨምሮ ብዝሃ ሕይወት የማይታሰብ በመሆኑ ደንን በመጠበቅ ሕይወትን ለማስቀጠል ከዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ስለመሠራታቸው አመላክተዋል።

አሁን ላይ ወቅቱ በጋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሰደድ እሳት ስጋት በመኖሩ ሕብረተሰቡ ለደኖች ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ያሉት የቡድን መሪው፣ ቀደም ተብሎ ግንዛቤ የተፈጠረ በመሆኑ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ለዚህ የተቋቋሙ 12 ግብረ ኃይሎች በሥራ ላይ መሆናቸውን ያመላከቱ ሲሆን የሰደድ እሳቱ ድንገት ቢከሰት ሳይዛመት ተረባርቦ መቆጣጠር ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ለስጋቱ ሰሞኑን በዞኑ ዞቄሳ ቀበሌ ተከስቶ የነበረውን ሕብረተሰቡ ተረባርቦ ተጨማሪ ውድመት ሳይደርስ መቆጣጠር መቻሉን እንደማሣያ ጠቁመዋል።

ነዋሪዎች ማንኛውንም እሳት ሲያቀጣጥሉ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውና ደንን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን