ጠንካራ ፓርቲ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ የፓርቲው አባላትና አመራር በአመለካከትና በተግባር አንድ ሆነው ሊሰሩ እንዲሚገባ ተጠቆመ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚዛን ማዕከል የብልጽግና ህብረት አባላት “ከቃል እስከ ባህል” በሁለተኛው የፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎች የቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በሚዛን አማን የውይይት መድረክ አካሂደዋል።

በሚዛን ማዕከል የሚገኙ የክልል ተቋማት አመራሮች የብልጽግና ፓርቲ ህብረት አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ህይወት አሰግድ እንደተናገሩት ብልጽግና ፓርቲ ከለዉጡ በኃላ እንደ ሀገር በፖለቲካዉ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና በዉጭ ግንኙነት ሰፊ ስራዎችን በመስራት ሀገርን ከብተና በመታደግ ሁለንተናዊ ብልጽግና እያረጋገጠ ያለ ፓርቲ ነዉ ብለዋል፡፡

እንደሀገር ያሉንን እምቅ አቅሞች በመጠቀም ብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ ተግባራዊ በማድረግ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በአይሲቲ ዘርፎች አመርቂ ዉጤት ማስመዝገብ የተቻለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር ሰላምን ለማረጋገጥ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸዉን የተናገሩት ወይዘሮ ህይወት፥ ችግር ከመፍታት ባሻገር የባህር በር የማግኛ ዕድሎችን ያሰፋንበት እና ወደ መጨረሻ ምዕራፍ የተደረሰበት ነው ብለዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የሚዛን ማዕከል ብልጽግና ህብረት ሰብሳቢ አቶ ጸደቀ ከፍታው በበኩላቸው “ከቃል እስከ ባህል” በሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ የማዕከሉ ብልጽግና ህብረት አባላት ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው ተናግረዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ከለውጡ ማግስት እንደ ሀገር የገጠመንን ፈተናዎች በጽናትና በጥበብ አልፎ ዛሬ ሀገርን ያስቀጠለ ትልቅ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።

የአባላትና አመራሩ ጠንካራ አቋምና አንድነት ለቀጣይ አቅጣጫዎች ስኬት ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ጸደቀ ሁሉም በተሰማራበት መስክ ግንባር ቀደም መሆን ይጠበቅበታል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም የፓርቲውን ውሳኔዎችና ቀጣይ አቅጣዎች ተፈጻሚ ለማድረግ አመራሩና አባላት ግንባር ቀደም በመሆን ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በተለይ አሁን ላይ በሀገሪቱ በኑሮ ውድነት፣ በዋጋ ንረት፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በጤና፣ በትራንስፖርት፣ በናፍጣና ቤንዚን እጥረት የሚታዩ ውስንነቶችን ለቅሞ መስራትና መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን