ባህላዊ እሴቶች፣ ታሪካዊ ቅርሶችና ተፈጥሮዊ ደኖችን በመጠበቅና በመጎብኘት ለትውልድ እንዲተላለፉ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

ሀዋሳ፡ የካቲት 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባህላዊ እሴቶች፣ ታሪካዊ ቅርሶችና ተፈጥሮዊ ደኖችን በመጠበቅና በመጎብኘት ለትውልድ እንዲተላለፉ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጥሪ አቅርቧል።

ቶቶት የወጣቶች ማህበር አባላት ለ6 ዙር የሃገርህን እወቅ ጉዞ መነሻቸውን አዲስ አበባ በማድረግ በጉራጌ ዞን የጌታ ወረዳ ተፈጥሮዊ ጥብቅ የዛራ ደን ጎብኝተዋል።

የቶቶት ማህበር ሰብሳቢ አቶ አንተነህ ኮሬ በዚህ ወቅት እንዳሉት በጉራጌ ዞን አካባቢ የሚገኙ ባህላዊ እሴቶች፣ታሪካዊ ቅርሶችና ተፈጥሮዊ ደኖችን በማስተዋወቅና በመጎብኘት ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ ነው።

ቶቶት የወጣቶች ማህበር ለ6ኛ ጊዜ የሃገርህን እወቅ ጉዞ ማድረጋቸውን ያነሱት አቶ አንተነህ፥ በጉራጌ ዞን የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች በጎብኘታቸውን ጠቁመው፥ ማህበሩ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን በመፈፀም እስካሁን ባከናወኗቸው ተግባራት በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውም አብራርተዋል።

እነዚህና መሰል የጉራጌ መገለጫዎች በማልማትና በመከባከብ ጠብቆ ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

የጌታ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ሰይፈ በበኩላቸው ዛራ ደን ከ1888 ዓ.ም በፊት ከአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት በፊት የነበረ እድሜ ጠገብ ደን ሲሆን ደኑም ከ30 ነጥብ 6 ሄክታር በላይ የሰፈረ መሆኑን አመላክተዋል።

ከ250 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ጽዶች፣ ዝግባ፣ ሾላ፣ የኮሶና ሌሎች ሀገር በቀል የተለያዩ ዛፍችና የዱር አራዊቶች እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

አቶ ሙሉጌታ አክለውም የዛራ ደን በየጊዜው ጥበቃ በማድረግ፣ በውስጡ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ በሀገርህን እወቅ ክበባት በማስጎብኘት፣ የጥናትና ምርምር ስራዎች እየተከናወነ ሲሆን በአሁን ሰአት በተለይ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኑን አስታውቀዋል።

ቶቶት የወጣቶች ማህበር በጌታ ወረዳ ጉብኝት ማድረጉ የወረዳው ጀግና አባት ፍታውራሪ ሳፎ ዴጀነን እንዲታወቁ የሚያደርግ እና ለዛራ ደን ለመልማት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አቶ መሉጌታ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ እንደተናገሩት ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮዊ መስህቦች በመጎብኘትና በማስተዋወቅ በኩል ቶቶት የወጣቶች ማህበር እያደረገ ያለውን ተሳትፎ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

አክለውም የቶቶ ማህበር በሚያከናውናቸው ተግባራቶችና በሚያስገኛቸው ውጤቶች ትልቅ እውቅና ያተረፈ ማህበር መሆኑን የገለፁት ወይዘሮ መሰረት፥ እነዚህና መሰል ስራዎች ፍሬ እንዲኖራቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተዋል።

አቶ ደማም ደላ እና አቶ ጌታቸው ሳህሌ የሀገር ሽማግሌዎች ሲሆኑ ደኑ የተጠበቀው ህብረተሰቡ ለደኑ ልዩ ጥበቃ በማድረግ እና ባህልን በመፍራት ጭምር ነው።

የዛራ ደን ለአካባቢው ማህበረሰብ ንጹህ አየር እንዲያገኝ ከማድረግ ባለፈ በተጨማሪ በርካታ የውሃ ምንጮች ፈልቀው ህዝቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ አስችሏል ነው ያሉት።

ይህ የቶቶት ሀገርህን እወቅ ጉዞ የጀግናው የፍታውራሪ ሳፎ ደጀን ታሪክ እንዲሁም የዛራ ደንን የበለጠ እንዲተዋወቅ የሚያደርግ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀው፥ ትውልዱ ባህሉ፣ ታሪኩን፣ ቅርሱን እና ወጉን መጠበቅ እንደሚኖርበት መክረዋል።

የቶቶት ማህበር አባላት በበኩላቸው የቀደምት አባቶች ያቆዩት ውብና ማራኪ የሆኑ ጥብቅ ተፈጥሮዊ የዛራ ደን በማየታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ በእርካብነሽ ወልደማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን