የአርሶ አደሩን የግብርና ቴክኖሎጂ ፍላጎት ለማሟላት የግብርና ምርምር ማዕከላትን ተደራሽነት ማስፋትና ማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርሶአደሩን የግብርና ቴክኖሎጂ ፍላጎት ለማሟላት የግብርና የምርምር ማዕከላትን ተደራሽነት ማስፋትና ማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንዳለው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሪሁን ፍቅሩ ገለጹ።

የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት የይርጋጨፌን የግብርና ምርምር ማዕከል ሥራ አስጀመሯል፡፡

ማዕከሉ በጌዴኦ፣ ኮሬና ቡርጂ ዞን የሚከናወኑ የግብርና ሥራዎችን ትኩረት አድረጎ የተለያዩ ምርምሮችን የሚያከናውን መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሪሁን ፍቅሩ፥ በክልሉ ግብርና ኢንስትቲዩት የይርጋጨፌ ምርምር ማዕከል ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፥ የአርሶአደሮች የቴክኖሎጂ ፍላጎት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የግብርና የምርምር ሥራዎችን የሚያከናውኑ ማከላት ተደራሽነት ማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በአዲስ መልክ የተቋቋሙውን የሳውላና የይርጋጨፌ ምርምር ማዕከላት ግብዓት የማሟላት ሥራ በማከናወን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡

የኢንስትቲዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ያሲን ጎአ የይርጋጨፌ ግብርና ምርምር ማዕከል ጌዴኦ፣ ኮሬና ቡርጂ ዞኖች ላይ የግብርና ምርታማነትን የበለጠ ለማሻሻልና በተፈጥሮ አያያዝ የሚስተዋሉ ማነቆዎች ላይ ምርምር በማካሄድ የአርሶአደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተቋቋመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ በቀጣይ የአርሶአደሮችን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ ከዚህ በፊት በአከባቢው በቡና ዘርፍ በተከናወኑ ሥራዎች ትልቅ ለውጥ መታየቱን ገልጸው፥ የይርጋጨፌ ግብርና ምርምር ማዕከል መቋቋሙ በቀጣይ በቡናና በእንሰት ዘርፍ በምርምር ሥራዎች በመታገዝ ዘርፉን ለማዘመንና የአርሶአደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) የክልሉ የግብርና ምርም ኢንስትቲዩት በዞኑና በአከባቢዋ ያለውን የተፈጥሮ ፀጋዎች በምርምር በመደገፍ ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር በአጭር ጊዜ ውስጥ በቡናና በእንሰት ዘርፍ የምርምር ሥራዎችን የሚያከናወን ማዕከል በማቋቋሙ አመስግነዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከአዋድ ምርምር ማዕከል ጋር እየሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፥ በቀጣይ ሁለቱን ማዕከላት አስተሳስሮ በመሥራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል፡፡

የይርጋጨፌ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አድማሱ ተፈራ ማዕከሉን በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባት ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን