በመንግስት ያልተሸፈኑ የልማት ስራዎችን በማገዝ ረገድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ የካቲት 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በመንግስት ያልተሸፈኑ የልማት ስራዎችን ክፍተት በመሙላትና በማከናወን ረገድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና አጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ።
የኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር ሐዋሳ ፕሮግራም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ የአራዳ ፕሮጀክት 164 ሚሊየን ብር በላይ ለሁለተኛ ጊዜ የሚተገበር መርሃ ግብር ይፋ አድርጓል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደር የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም አበበ እንዳሉት፥ ድርጅቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ከዛሬ 75 ዓመታት በፊት በኦስትሪያ የተመሰረተ መሆኑን ጠቁመው፥ በኢትዮጵያ ላለፉት ሀምሳ ዓመታት በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በህጻናት፣ በወጣቶች፣ በቤተሰብ እና በማህበረሰብ ማጠናከሪያ ዙርያ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እንደ ሀገር ድርጅቱ እስከአሁን በወጣቶች ላይ በሰራቸው ስራዎች 4 ሺ 800 ወጣቶች ምንም ከሌለበት ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረጉን ጠቅሰው፥ በቤተሰብ እና ማህበረሰብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ከአንድ ሚሊየን በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚዎች ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በተለያዩ ወቅቶች ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል።
የአራዳ ፕሮጀክት በመጀመሪያው ዙር ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጾ ያደረጉ አካላትንም አቶ ሳህለማሪያም አመስግነዋል ።
በኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደር የሐዋሳ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ ደጀኔ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ለቀጣዮቹ ሶስት አመታት የሚቆይ መሆኑንና ለተግባሩም ከ164 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ገልጸዋል ።
በፕሮጀክቱ በ2ኛዉ ዙር 1 ሺህ 500 ህፃናት፣ 100 ወጣቶች፣ ከ300 በላይ ቤተሰቦች በዋነኛነት ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ ተናግረዋል ።
በኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደር የሐዋሳ ፕሮግራም የቤተሰብ እና ማህበረሰብ ማጠናከሪያ መርሃ ግብር ማናጀር አቶ ተክሉ አርጋው እንዳሉት በፕሮጀክቱም ከ10 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ አስረድተዋል ።
በኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር የአራዳ ፕሮጀክት ኦፊሰር የሆኑት ወይዘሮ ቅድስት ወንድዬ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም በሆሳዕና ከተማ በአራዳ ቀበሌ ብቻ ተግባራዊ ሲደረግ እንደ ነበር ጠቅሰው በሁለተኛ ዙር ግን የሴች ዱና ቀበሌን ጨምሮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
በእለቱ የተገኙት የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ታሪኩ ተከተል እንዳሉት ድርጅቱ በሆሣዕና ከተማ እያደረገ ያለው ተግባር የተሳካ እንዲሆን እንደከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊ ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ አንዳንድ አካላት በሰጡት አስተያየት ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር የትውልድ ቀጣይነትን የሚያረጋግጡ ተግባራትን እያከናወና እንደሚገኝ ጠቅሰው ይህም በመንግስት የማይሸፈኑ የልማት ስራዎችን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እየሸፈኑ መሆናቸውን ማሳያ በመሆኑ ሌሎች አጋር አካላትም መሰል ተግባራትን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ የመጀመሪያ ፕሮጀክት በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው ሲሆን በቀጣይ በሚተገበረው ፕሮጀክት ዙሪያም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል ስምምነት መፈራረም ተችሏል።
ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ
ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገለፀ
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሀገሪቱ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባ ተገለፀ