የአርቶ ፍል ውኃ ለበጋ መስኖ ልማት አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ሀዋሳ፡ የካቲት 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርቶ ፍል ውኃ በአዲስ መልክ ለበጋ መስኖ ልማት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በሀላባ ዞን የዌራ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ።
በመስኖ ልማት ሥራው ተጠቃሚ መሆናቸውን የአከባቢው አርሶ አደሮች ገልፀዋል።
በሀላባ ዞን የዌራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል ሚሓሌ የኣርቶ ፍል ውኃ ለዘመናት ለመድሃኒትነት ብቻ ሲያገለግል መቆየቱን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ ይህን የአርቶ ፍል ውኃ ከፈውስነት ባለፈ ለግብርና ልማት ሥራ ለማዋል በተጠነሰሰው ሀሳብ መነሻ በዘንድሮው ዓመት በስፋት ወደበጋ መስኖ ልማት ሥራ መገባቱን ተከትሎ ከ25 በላይ ሄክታር መሬት እየለማ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ምን አልባት ፍል ውኃው የጎንዮሽ የጤና እክል የሚያስከትል አለመሆኑን ለማረጋገጥ ቀደም ሲል ተደጋጋሚ የሳምፕል ምርመራ በሀገር ደረጃ ተደርጎ ምንም አይነት ጉዳት የሚያስከትል አለመሆኑም ተረጋግጧል ብለዋል።
በመሆኑም በዘንድሮው የበጋ መስኖ ዘመቻ የተለያዩ የአዝርዕት ሰብሎችን ማለትም የበቆሎ፣ የሽንኩርት፣ የቲማትም፣ የጎመን፣ የቃሪያና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የምርት ውጤቶችን በማልማት ሂደት ላይ መሆኑን ኃለፊው ጠቁመዋል።
በዚህም ፍል ውኃውን በአጭር ጊዜ ማቀዝቀዝ ለማስቻል እና በተፈለገ ወቅት ሁሉ ልማት ላይ ለማዋል ዘመናዊ የማቀዝቀዣ ማሽን በመጠቀም ከዋናው ተፍለቅላቂ ውኃ ዘውትር ምሽት ወደ ሌላ ማቆሪያ ቦታ በፓምፐር በመሳብ ለልማት የማዋል ተግባር ላይ ስለመገኘታቸውም አቶ ጀማል አብራርተዋል።
በአከባቢው ኢንቬስተሮችን ብሎም አልሚ ወጣቶችን በማህበር በማደራጀትና አስፈላገውን ድጋፍ በማድረግ በስፋት ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በአሁኑ ሰዓት በተመቻቸላቸው የገበያ ትስስር የልማት ትሩፋቶችን ለገበያ እንዲያቀርቡ የማስቻል ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ኃላፊው ገልፀዋል።
አቶ ጀማል አክለውም ይህ ፍል ውኃ ከሌሎች የውሃ አማራጮች በባህሪው ለየት የሚያደርገው ምንም ዓይነት የውኃ እጥረት ሥጋትና መጠነ መቀነስ የማይስተዋልበት መሆኑን አመላክተዋል።
የሥራ ባህላችንን ይበልጥ በማጠናከር ከዓመት እስከ ዓመት በማይጎድለው የአርቶ ፍል ውኃ በዓመት ከአራትና ከዛ በላይ ጊዜ ማልማት እንደሚቻል ኃላፊው ጠቁመዋል።
ይህ ኢኒሼቲቭ ከዚህ ቀደም ያልተሞከረና ያልነበረ በመሆኑ ለበርካታ ዓመታት ለዚህ ዓላማ ሳንጠቀም መቆየታችን የሚያስቆጭ ነው ያሉት አቶ ጀማል እንደ ሀገር በተያዘው አቅጣጫ በግብርናው ዘርፍ ይበልጥ ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በብልሃት መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
በአከባቢው የሚገኙ የበጋ መስኖ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ፍል ውኃውን በመጠቀም በአዲስ መልክ በተጀመረው የበጋ መስኖ ልማት ሥራ ዘርፈ ብዙ ሰብሎችን በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከተጠቃሚ አርሶ አደሮቹ መካከል ሞዴል አርሶ አደር የሆኑት አቶ ፉዓድ አብደላ የአርቶ ፍል ውኃን በመጠቀም የሚከናወነው የበጋ መስኖ እንቅስቃሴ ከዓመት እስከ ዓመት ያለምንም መቆራረጥ ለማልማት መዘጋጀታቸውን ገልፀው ከራስ ተርፈው በስፋት ለገበያ የማቅረብ ሥራ ለመሥራት በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀሱ አብራርተዋል።
ዘጋቢ: አብዱልሰመድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የስራ ስር ሰብሎች የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተጠቆመ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በይፋ ተጀመሯል
በመስኖ ሥራ የተሰማሩ የኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች የተለያዩ ሰብሎችን በጥራትና በብዛት በማምረት የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡