የውሃ አማራጮችን ተጠቅመው የተለያዩ ፍራፍሬና የጓሮ አትክልቶችን አምርተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን በዳውሮ ዞን ከጪ ወረዳ የቦካ ክላስተር አርሶ አደሮች ገልጸዋል
በወረዳው እየተሠሩ ያሉ የመስኖ ተግባራት ከአምራቾች ተጠቃሚነት ባለፈ የአካባቢ ገበያን በማረጋጋት ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኝ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አስታውቀዋል።
በወረዳው የቦካ ክላስተር መሬታቸው በተፈጥሮ እርጥበት ያለው በመሆኑ ይህንን ተጠቅመው አርሶአደሮች በተለይም የበቆሎ ምርት በአመት 3 ጊዜ በማምረትና በፍራፍሬ ዘርፍም ለአካባቢና ከዛም ባለፈ ከፍተኛ ምርት በማቅረብ የሚታወቅ አካባቢ ሲሆን ባለው ምቹ ሁኔታ ላይ የዝናብ እና መስኖንም በመጠቀም በበጋ እርሻ ስራ ላይም በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኙ አቶ አለማየሁ አይሳ እና ወጣት ኤሊያስ አበራ ተናግረዋል።
በአካባቢው ዘመናዊ የመስኖ አውታር ከተዘረጋ ጀምሮ ከጓሮ አትክልቶች ቲማትም፣ ጎመን፣ ካሮትና ቀይስር ከፍራፍሬ ደግሞ ምርጥ ዘር ሙዝ፣ አቦካዶ እና የበቆሎ ሰብልም እያመረቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ዘንድሮም ከአንድ ሄክታር በላይ ማሳ በቴክኖሎጂ ታግዘው ቲማትም እና ፍራፍሬ እያመረቱ እንደሚገኙ ገልፀው በዚህም የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውንና በቤታቸውም ለምግብነት እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ነው የጠቀሱት።
ለተግባራቸው የግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ እገዛ እያደረጉላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
የገበያ ፍላጎትም ከፍተኛ በመሆኑ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን ተጠቅመው በቀጣይ አስፍተው ለመስራት መቁረጣቸውንም አርሶአደሮቹ ገልጸዋል።
አካባቢውን የአትክልትና ፍራ ፍሬ ክላስተር ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ የኮማ ጉንቻ ቀበሌ ግብርና ባለሙያዎች አስተባባሪ አቶ ገዛኸኝ ገሉ ገልጸው አርሶአደሮች ምርትና ምርታማነታቸውን አሳድገው የምግብና የገበያ ፍላጎትም እንዲያሳድጉ ትኩረት ተሰጥቶበታል ብለዋል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ውለታው ሁሴን በበኩላቸው በወረዳ ደረጃ 4 ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችና ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም አርሶ አደሮች የበጋ እርሻ ላይ በስፋት እንዲሳተፉ ለማስቻል ከወረዳ አስተባባሪ ጀምሮ እስከ ቀበሌ ባለሙያ ድረስ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በበጋ መስኖ የተሻለ ምርት እየተገኘ መምጣቱን ጠቅሰው በተለይም በጓሮ አትክልት ዘርፍ ከሌላ ቦታ የሚጫነውን ምርት በአካባቢው ለመሸፈንና አርሶአደሮችም በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ እንደሚገኝም ነው አስተዳዳሪው የገለፁት።
አርሶ አደሮች በበጋ እርሻ በስፋት መሳተፍ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉና የምግብ ዋስትናቸውንም እንዲያረጋግጡ የሚያስችል በመሆኑ በዘርፉ የሚደረገው ድጋፍና ግንዛቤ የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ውለታው ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
ሳታ ቴክኖሎጂ እና ቢዝነስ ኮሌጅ በአርባ ምንጭ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያ ዲግሪ እና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 132 ተማሪዎችን አስመረቀ
በዕቅድ የሚመራ የመፈፀም አቅሙ ያደገ ሲቪል ሰርቫንት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን በደቡብ ኦሞ ዞን የሳላማጎ ወረዳ ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት ገለፀ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከውጭ ይገቡ የነበሩትን ሰብሎች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰመስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው አስታወቁ