በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ

በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ

መምሪያው የ2017 በጀት ዓመት የማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ጥምረት አስተባባሪዎችና ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት የግማሽ አመት አፈፃፀም ግምገማ አካሂዷል፡፡

መድረኩን የመሩት የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ምህረቱ ተፈሪ፤ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ የባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በከተማም ሆነ በገጠር ለችግር የተጋለጡ አካላትን ለመደገፍ ማህበረሰቡን መሰረት ያደረገ የሀብት አሰባሰብና አጠቃቀም ስርዓት ለመዘርጋት የተቋቋመው የማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ጥምረት ኮሚቴ በማቋቋም ወደተግባር መግባታቸውን በመድረኩ የገለፁት የጌዴኦ ዞን ሠራተኛና ማህራዊ ገዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ፍሬነሽ አየለ ናቸው፡፡

ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመለየት በዞኑ በተሰራ ጥናት የመሬት ወረራ፣ ድርብ ጋብቻና በኢኮኖሚ መጥኖ አለመውለድ የሚጠቀሱ ምክንያቶች መሆናቸውን ወ/ሮ ፍሬነሽ በመግለፅ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የ6 ወር አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የዞኑ ሰራተኞችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ማህበራዊ ችግሮችን መከላከል ስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ከበደ ክርስቶ፤ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመርዳት ከአካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን፣ ከበጎ አድራጎት ማህበራት፣ ከሀይማኖት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ጥምረቱ በ6 ወር አፈፃፀም በጥንካሬ የተከናወነ ተግባራትን በማጎልበት ጉድለቶችን አርሞ በቀጣይ በበለጠ ለመስራት ትኩረት እንደሚያደርጉ የተናገሩት አቶ ከበደ፤ መምሪያው በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ: ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን