ከ36 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህጻናት የፖሊዮ ክትባት ለማዳረስ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የኮሬ ዞን ጤና ዩኒት ገለጸ

ከ36 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህጻናት የፖሊዮ ክትባት ለማዳረስ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የኮሬ ዞን ጤና ዩኒት ገለጸ

ዩኒቱ የክትባቱን ሂደት ለማሳለጥ ለሚመለከታቸው አካላት ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።

የኮሬ ዞን ጤና ዩኒት የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አሸናፊ ሻርዳ፤ የፖሊዮ በሽታ ክትባትን ህጻናት ካልወሰዱ ለአካል ጉዳትና ለሞት የሚዳርግ እንደሆነ ተናግረዋል።

በመሆኑም በዞኑ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ከየካቲት 14/2017 ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት ክትባቱ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በተግባሩ ላይ ለሚሳተፉ ባለድርሻዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት አቶ አሸናፊ፤ በየደረጃው ስልጠናው ከተሰጠ በኋላ ወደተግባር የሚገባ እንደሆነም አመላክተዋል።

በዘመቻው ከ36 ሺህ በላይ ህጻናት እንደሚከተቡና ከዚህ በፊት የተከተቡትንም የሚያካትት በመሆኑ ህብረተሰቡ እንዲተባበር አሳስበዋል።

የዞኑ ጤና ዩኒት አስተባባሪ አቶ ደመላሽ ሽፈራው በበኩላቸው፣ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንና በተቀናጀ መልኩ ቤት ለቤት የሚሰጥ መሆኑን አመላክተዋል።

የመጀመሪያ ዙር ለተቋማት ኃላፊዎችና ሱፐርቫይዘሮች ስልጠናው የተሰጠ ሲሆን በየደረጃው የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል፡፡

ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን