የሀገር ተስፋ ከዳር እንዲደርስ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ድርሻ ላቅ ያለ መሆኑ ተገለፀ

የሀገር ተስፋ ከዳር እንዲደርስ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ድርሻ ላቅ ያለ መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀገር ተስፋ ከዳር እንዲደርስ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ድርሻ ላቅ ያለ መሆኑን የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳዊት ሃዬሶ ገለጹ፡፡

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ለ14ኛ ዙር በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመደበኛና በተከታታይ የተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 513 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ፕሮግራም ላይ የተገኙት የዕለቱ የክብር እንግዳ የሀዲያ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር በፍቃዱ ገ/ሃና በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገራት የትምህርት ስርዓትን በማዘመንና በማስፋፋት ለልማትና ዴሞክራሲ ማበብ የተለየ ሚና እንዲጫወት አድርገዋል ብለዋል።

ትምህርትና ስልጠና ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ ስለሚወጣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኳቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች ከጠባቂነት አመለካከት በመላቀቅ በተለያዩ አደረጃጀቶች በመታገዝ ስራ በመፍጠር የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋፅኦ መወጣት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዛሬው ዕለት በዩኒቨርሲቲው በጤና ሰይንስ ኮሌጅ የተመረቁ ተመራቂዎች የታመሙትን በመፈወስ፣ የተጎዱትን በመንከባከብ እና ተስፋ የቆረጡትን በማበረታታት ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳዊት ሃዬሶ በበኩላቸው በሚማሩበት ወቅት ሁለንተናዊ ድጋፍ ላደረገላቸው ቤተሰብና ማህበረሰብ የተለየ አበርክቶ በማድረግ የዜግነት ግዴታ መወጣት እንዳለባቸው አንስተዋል።

ለሰላምና ሁሉ አቀፍ ዕድገት የትምህርት ዘርፍ ሚና ላቅ ያለ ስለ መሆኑ የገለፁት ዶ/ር ዳዊት፥ የትምህርት ሂደቱ ከተቃና የሀገር የዕድገት ጉዞ ፈጣን ይሆናል ብለዋል።

የዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት በመማር ማስተማር ወቅት ብዙ ውጣ ውረዶችን ቢያሳልፉም ለያዙት ዓላማ በመፅናት ለውጤት መብቃታቸውን ጠቁመው፥ በተማሩት የሙያ ዘርፍ ማህበረሰቡን በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ዘጋቢ: ዳኜ አየለ – ከሆሳዕና ጣቢያችን