ተመራቂ ተማሪዎች ከመንግስት ተቀጣሪነት ይልቅ ለስራ ፈጣሪነት ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው ተገለጸ

ተመራቂ ተማሪዎች ከመንግስት ተቀጣሪነት ይልቅ ለስራ ፈጣሪነት ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ተመራቂ ተማሪዎች ከመንግስት ተቀጣሪነት ይልቅ ለስራ ፈጣሪነት ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ፍሰሀ ይታገሱ ተናገሩ።

ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ እና በድህረ ምረቃ ፕሮግራም ያስተማራቸውን 394 ተማሪዎቹን ለ17ኛ ጊዜ አስመርቋል።

ሁለተኛ ትውልድ እየተባሉ ከሚጠሩት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ፥ ከዛሬ አስራ ስምንት አመት በፊት 200 መቶ ተማሪዎችን ተቀብሎ አስተምሮ ያስመረቀ ሲሆን ዘንድሮም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 394 ተማሪዎችን በድህረ ምረቃ እና በመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም ማስመረቁን ነው የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዋቆ ገዳ የተናገሩት።

ዩኒቨርስቲው በዘንድሮ 2017 የትምህርት ዘመን በ54 ቅድመ እና በ42 ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን እያስተማረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በዩንቨርስቲው የነበሩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንደ ሀገር ትምህርት ሚኒስቴር የሰራው ሀገራዊ የሪፎርም ስራ የዩኒቨርስቲ አመራር ቦርዶች በአዲስ በመተካቱ የነበሩ ጉድለቶችን በማረም ያሉትን ጥንካሬዎች በማስቀጠል በተሰሩት ስራ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገብ ተችሏልም ብለዋል።

ዩኒቨርስቲው በ2017 የትምህርት ዘመን ከ80 በመቶ በመረጡት የትምህርት ዘርፍ መደልደል መቻሉን ጠቁመው ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና የተሻለ ውጤትም እንዲያስመዘግቡ በመምህራኖች በሚሰጣቸው ድጋፍም የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማድረጉን ገልጸዋል።

በምረቃው ስነ-ስረአት ላይ የተገኙት የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ፍሰሀ ይታገሱ በበኩላቸው፥ የሀገራችን መንግስት በትምህርቱ ዘርፍ የነበሩ ስብራቶችን ለመጠገን በርካታ የሪፎርም ስራዎችን መስራቱን ጠቁመው፥ በአጭር ጊዜ ቀላል የማይባሉ ለውጦች መመዝገብ ችሏል ብለዋል።

ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ላለፉት አመታት በሀገር አቀፍ የመውጪያ ፈተና ያስመዘገበው አመርቂ ውጤት የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እና መምህራን የጋራ ውጤት በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

ምሩቃን ተማሪዎች ወደ ሰፊው ማህበረሰብ ስትቀላቀሉ ከመንግስት ተቀጣሪነት አስተሳሰብ ይልቅ ለስራ ፈጣሪነት ትኩረት ማድረግ ይገባችኋል ብለዋል።

ዩኒቨርስቲው ከምሩቃኑ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ነጥብ ላመጡ ሁለት የጤና ተመራቂ ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል ሰጥቷል።

ከፍተኛ ውጤት አምጥተው የተመረቁ ተማሪዎችም ዩኒቨርስቲው በሰጣቸው ነጻ የትምህርት እድል መደሰታቸውን ጠቁመው ህብረተሰባቸውን በሰለጠኑበት ሙያ ለማገልገል ቃል ገብተዋል።

እንዲሁም በመንግስት የትምህርት እድል ተጠቃሚ የሆኑ እና በድህረ ምረቃ የተመረቁ የአመራር አካላቶችም ባገኙት እውቀት ይበልጥ ህብረተሰባቸውን ለማገልገል ቃል ገብተዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን