የጎፉ ዩንቨርሳል ኮሌጅ ለ18ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

የጎፋ ዩንቨርሳል ኮሌጅ ለ18ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጎፋ ዩንቨርሳል ኮሌጅ ለ18ኛ ዙር በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች በድግሪና ዲፕሎማ መርሃ-ግብር ያስተማራቸውን 570 ተማሪዎች አስመረቀ፡፡

ተቋሙ ከፍለው የመማር አቅም ለሌላቸው 20 ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ማመቻቸቱን የኮሌጁ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ፕ/ር እያሱ ኤልያስ በመርሃ-ግብሩ ላይ ገልጸዋል።

የጎፋ ዩንቨርሳል ኮሌጅ ዲን አቶ ዘላለም ዘካሪያስ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ኮሌጁ ለ18ኛ ዙር በድግሪ 186 በዲፕሎማ 384 በድምሩ 570 ተማሪዎችን ለምረቃ አብቅቷል።

የጎፋ ዩንቨርሳል ኮሌጅ ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባበት ከ1998 ዓ.ም አንስቶ ላለፉት 19 አመታት በተለያዩ የሞያ መሥኮች ጥራት ያለው ስልጠናና በመስጠት ከ7ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቅ መቻሉን የኮሌጁ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ፕ/ር እያሱ ኤልያስ አብራርተዋል።

በዚህኛው ዙር በመንግስትና በተቋሙ በኩል ከፍለው የመማር አቅም ለሌላቸው 20 ተማሪዎች እንዲሁም ኮሌጁ ከተመሠረተ አንስቶ በድምሩ ከ5መቶ በላይ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ማመቻቸት መቻሉንም ጠቁመዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው፤ ኮሌጁ በአካባቢው ይስተዋል የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነት ችግር ከመፍታት አኳያ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

ኮሌጁ በቀጣይም የትምህርት ጥራቱን በማሻሻል ይበልጥ አቅሙን ለማጎልበት ለሚያደርገው ጥረት የዞኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አስተዳዳሪው አረጋግጠዋል።

ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የሙያ መሥክ ስራ ፈጣሪ በመሆን ለሐገራቸው የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ነፃ የትምህርት እድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል በሰጡት አስተያየት፤ ባገኙት እድል መደሰታቸውን ገልጸው ለኮሌጁ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተለያዩ የሙያ መሥኮች የተመረቁ ተማሪዎችም በተማሩበት የሙያ መሥክ ህብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን