ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ በርካታ አወንታዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ
ሀዋሳ፡ የካቲት 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ በርካታ አወንታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
ርዕስ መስተዳድሩ ይህን ያሉት ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን መንግሥት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ የክልሉ መንግሥት ከክልሉ ህብረተሰብ ጋር በመቀናጀት በርካታ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
እንደሀገር የመጣውን ለውጥና ሪፎርም ቀጣይነት ማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስረፅ፣ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ በልዩ ትኩረት የተሰሩ ተግባራት ናቸው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
ለሰው ሰራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት፣ ሰላምና ፀጥታን በመላው ክልሉ ማስፈንና የህብረተሰቡን ደህንነት መጠበቅ ውጤታማ የነበሩ ተግባራት እንደሆኑ ጠቁመዋል።
በግብርናው ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ሂደቱ ውጤት በተጨባጭ ማምጣቱ፣ በሰብል ልማት ዘርፍ ለስፔሻላይዜሽን ትኩረት መሰጠቱ፣ ለአረንጓዴ ልማትና በደን ሽፋን ማሳደግ ረገድ የሚታዩ ለውጦች መመዝገባቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።
ለትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ህብረተሰቡን በማሳተፍ የሟሟላት ተግባር፣ የህብረተሰብ ጤና መድህን ሽፋን ተጠቃሚዎችን ማሳደግ፣ የወባ ወረርሽኝን መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም ለጤና ተቋማት የጤና ግብአቶችን አቅም በፈቀደ መጠን ሟሟላት የግማሽ አመቱ የክልሉ መንግሥት ስኬቶች ናቸው ብለዋል።
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጎልበት፣ የተሻለ የገቢና የገበያ ስርዓትን በመዘርጋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የከተማና የኢንዱስትሪ ልማትን ማፋጠን፣ የመሠረተ ልማትና የማህበራዊ መገልገያ አገልግሎቶችን በፍትሃዊነት ለማዳረስ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን አቶ ጥላሁን አረጋግጠዋል።
የገበያ ማረጋጋት እና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት፣ የነዳጅ አቅርቦትና አስተዳደር፣ ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ እንዲሁም የገቢ አሰባሰብ በሚጠበቀው ልክ ውጤታማ ያልሆኑ አፈፃፀሞች ናቸው ብለዋል አቶ ጥላሁን ከበደ።
የተወሰኑ ተግዳሮቶች ያሉ ቢሆንም በጥቅሉ በመላው ህብረተሰብ ተሳትፎ በበርካታ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ