ከተረጂነት በመላቀቅ በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ርብርብ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ
የጌዴኦ ልማት ማህበር የወል መሬት በመኸር እርሻ ያለማውን የስንዴ ምርት የማሰባሰብ ሥራ ማከናወን መጀመሩ ተገልጿል፡፡
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደ ሀገር የተቀመጠውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ በዞኑ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትልና እርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በድሉ አየለ ገልጸዋል፡፡
ከተረጂነት በመላቀቅ በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ርብርብ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መምጣታቸውንም አስረድተዋል፡፡
በመኸር እርሻ የለማውን ስንዴ ምርት ጊዜን፣ ጉልበትንና የእህል ብክነትን ለመቀነስ በቴክኖሎጂ በመታገዝ መሰብሰብ መጀመሩን አቶ በድሉ ገልጸዋል፡፡
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አምራቾች ሙሉ የግብርና ፓኬጅ እንዲጠቀሙ የልማት ባለሙያዎች ግንዛቤ በማስጨበጥ ክትትልና ድጋፍ በማድረጋቸው ቀድሞ ከነበረው የተሻለ ውጤት መመዝገቡን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ይህን ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የጌዴኦ ልማት ማህበር በትምህርት፣ በጤናና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ይሳተፍ እንደነበር ያስታወሱት የልማት ማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ ንጉሴ፤ በግብርናው ዘርፍም በመሳተፍ በጮርሶ ወረዳ በዘመናዊ እርሻ በመታገዝ ያመረተው ስንዴ ለምርት መድረሱን አብራርተዋል፡፡
በአዳሪ ትምህርት ቤት ልማት ማህበሩ ለሚያስተምራቸው ተማሪዎች ከገበያ የሚገዛውን ስንዴ ፍጆታ ከእርሻ ለማግኘት በማቀድ በመኸር ወቅት ያመረተውን ስንዴ በኮምባይነር እየሰበሰቡ መሆናቸውን አቶ ብዙነህ ተናግረዋል፡፡
የጮርሶ ወረዳ የግብርና ልማት ባለሙያ አቶ አብርሃም ከፍያለው በበኩላቸው፤ ለአርሶአደሩ በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲያመርት ግንዛቤ ማስጨበጫና ትምህርት በመስጠት ከእርሻ ዝግጅት ምዕራፍ እስከ ምርት መሰብሰብ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ማደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከልማት ባለሙያዎች ባገኙት ግንዛቤ መሬትን አለስልሰው በመስመር የዘሩት ስንዴ ምርቱ አስደሳች መሆኑን ከወረዳው አርሶአደሮች መካከል አዲሱ ታደሴ እና ገመቹ ሮቤ ተናግረዋል፡፡
በልማት ማህበሩ በቀበሌያቸው በተጀመረው ዘመናዊ እርሻ የተሻለ ምርት በመገኘቱ በቀጣይ አርሶ አደሮቹ በኩታ ገጠም በመደራጀት ያዩትን በተግባር ለማዋል ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ከመግፋፋት በመውጣት የመደመር ዕሳቤን በማጎልበት በህዝቦች መካከል ያሉ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስክ ያስተማራቸውን 518 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል አለው – ሚ/ር ዴኤታ የትምጌታ አስራት