ከ36 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በበልግ አዝመራ እንደሚሸፈን በምዕራብ ኦሞ ዞን የመኤኒት ጎልዲያ ወረዳ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ስራ ጽ/ቤት ገለጸ
በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮችም ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማሳ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የጽ/ቤቱ ምክትል ሀላፊና የእርሻና ሕብረት ስራ ዘርፍ ምክትል ሀላፊ አቶ አዳነ አበበ እንደገለፁት፤ 36 ሺህ 650 ሄክታር ማሣ ተለይቶና ዝግጅት ተደርጎ ትግበራ ተጀምሯል።
በዚህም 34 ሺህ 500 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 6 አልሚ ባለሀብቶች በመካናይዜሽን በመጠቀም እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ቀድሞ በልግ በሚገባባቸው ቀበሌዎች ላይ 1250 ሄክታር በላይ ማሣ በበቆሎ ሰብል ተሸፍኗል ብለዋል አቶ አዳነ።
ለበልግ አዝመራ ከአምስት መቶ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ለመጠቀም ዝግጅት መደረጉን አቶ አዳነ ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 3771 ኩንታል ግብዓት በገጠር ቀበሌ ግብዓት ማከማቻ መድረሱን አብራርተዋል።
በበልግ አዝመራ አብዛኛው ማሳ በበቆሎ ሰብል እንደሚሸፈን የጽ/ቤቱ ምክትል ሀላፊው ጠቁመው ሰሊጥ፣ ሩዝና በሎቄ በኩታ ገጠም እንደሚታረስም አስረድተዋል።
በወረዳው የበቆሎ ምርታማነት በሄክታር ከ60 እስከ 80 ኩንታል፣ ሰሊጥ በሄክታር ከ4 እስከ 7 ኩንታል መሆኑን አቶ አዳነ አንስተው ከዚህ በላይ መገኘት እንዲችል የክትትልና ድጋፍ ስራ ተጠናክሮ ይሰጣል ብለዋል።
በሚዛን ዕፅዋት ጥበቃ ክሊኒክ ማዕከል የእጽዋት በሽታ ጥናት ምርምርና መከላከል ባለሙያ የሆኑት አቶ ይታይ ወልደትንሳኤ በበኩላቸው፤ በመኤንት ጎልዲያ ወረዳ የበልግ አዝመራ ቅድመ ዝግጅትና መወሰድ ባለበት ጥንቃቄ ላይ በሰብል ተባይና አረም ክትትልና ቁጥጥር ላይ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዘንድሮው የበልግ አዝመራ ጸሐይ ወቅት የተራዘመበት በመሆኑ ለማሳ ዝግጅት ምቹ ቢሆንም ለበቆሎ ተምች መከሰት ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ስለሚችል ሰብሉ እንዳይጠቃ አርሶ አደሩ በባህላዊ መንገድ እንዲከላከል ካልሆነም ኬሚካል በመጠቀም እንዲከላከል አስገንዝበዋል።
ካነጋግረናቸው አርሶአደሮች መካከል አርሶ አደር ጌታሁን ሳፒ እና አርሶ አደር አንድነት ደምሴ፤ የአምናው የበልግ አዝመራ ዝናብ የበዛበትና ለአረም የተጋለጠ እንዲሁም ምርቱ ዝቅተኛ እንደነበር አውስተው የዘንድሮ ጸሐይ ለማሳ ዝግጅት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ በመሆኑ በቂ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በተለይ በአሁን ጊዜ በገበያ ላይ ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣውን ሰሊጥ በኩታገጠም እርሻ ሜካናይዝድ አስተራረስ ዘዴ በመጠቀም እየተዘጋጁ እንደሆነም አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
ሳታ ቴክኖሎጂ እና ቢዝነስ ኮሌጅ በአርባ ምንጭ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያ ዲግሪ እና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 132 ተማሪዎችን አስመረቀ
በዕቅድ የሚመራ የመፈፀም አቅሙ ያደገ ሲቪል ሰርቫንት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን በደቡብ ኦሞ ዞን የሳላማጎ ወረዳ ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት ገለፀ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከውጭ ይገቡ የነበሩትን ሰብሎች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰመስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው አስታወቁ