በአስር አመቷ ታዳጊ ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ በ15 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ
ሀዋሳ፡ የካቲት 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአስር አመቷ ታዳጊ ላይ አካላዊ ጉዳት እና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈጸመው የሀያ ሁለት አመቱ ግለሰብ በአስራ አምስት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን በቤንች ሸኮ ዞን የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር አቃቤ ህግ አስታወቀ።
በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የአዲስ ከተማ ቀበሌ ነዋሪ የሆነችው ታዳጊ አብረኸት አረፈ አይኔ የተባለችው የአስር አመት ታዳጊ ለቤተሰቦቿ ውሃ ለመቅዳት ወደ ወንዝ በወረደችበት ወቅት ወንጀለኛው የዚሁ የአዲስ ከተማ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ብሩክ ወይንም በቅጽል ስሙ ማሙሽ አድማሱ የተባለው የ22 አመት እድሜ ወጣት ያለፍላጎቷ መስከረም 14 ቀን 2017 አመተ ምህረት ከጥዋቱ 10 ሰአት አከባቢ እገልሻለሁ ብሎ ካስፈራራት በኋላ አካላዊ ጥቃትና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ከፈጸመ በኋላ ይህንንም ለማንም እንዳትናገር በጩቤ አውጥቶ አንገቷ ስር በማድረግ ካስፈራራት በኋላ መሰወሩን የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር አቃቤ ህግ አቶ ጥላሁን ቢኒያም ለችሎቱ አስረድተዋል።
ተበዳይ ታዳጊዋ ጥቃቱ ቢደርስባትም ህመሟን ደብቃ ለቤተሰቦቿ ሳትናገር መቆየቷን የጠቆሙት አቃቤ ህጉ፥ ወንጀለኛው በድጋሚ ቤተሰቦቿ ለቅሶ ለመድረስ ከቤት መውጣታቸውን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ በድጋሚ መስከረም 26 2017 ከጥዋቱ 4 ሰአት በድጋሚ ሊደፍራት መምጣቱን አስረድተው፥ ታዳጊዋ ባሰማችው የድረሱልኝ ጩኸት ለፖሊስ በሰጠችው ጥቆማ ወንጀለኛው በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
ታዳጊዋ በደረሰባት ጥቃት በወቅቱ ህክምና አለማግኘቷ ጉዳቷን የከፋ እንዳደረገው እና ከሚዛን ጤና ጣቢያም ወደ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል በሪፈር መሄዷን የገለጹት አቃቤ ህጉ በዛም በተደረገላት ህክምና በተወሰነ ደረጃ ህመሟ ማገገሙ ተናግረው አሁንም ህክምና እየተከታተለች መሆኗን አስረድተዋል።
ወንጀለኛው በታዳጊዋ ላይ ያደረሰው የአካል ጥቃትና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ምርመራ ሲከታተል የነበረው ፖሊስ መዝገቡን ለአቃቤ ህግ ማስተላለፉን ተከትሎ አቃቤ ህግም በወንጀለኛ መቅጫ 627 ንኡስ አንቀጽ 1 ክስ መመስረቱን ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ ክሱን እንዲከላከልና የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቢጠየቅም መከላከያ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 627 ንኡስ አንቀጽ ለወንጀለኛው ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ የካቲት 5/2017 ባስዋለው ችሎት በ15 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል።
የተጎጂዋ ወላጅ እናትም በሰጡት አስተያየት በበኩሏ በግለሰብ ቤት ልብስ እያጠበች በችግር ያሳደገቻትን ህጻን ልጅዋን በዚህ አይነት መልኩ ጥቃት እና ጉዳትን ማስተናገዷ እንዳሳዘናት ገልጻ፥ በጥፋተኛው ላይ የተወሰነው የህግ ውሳኔ ጥሩ እንደሆነም ተናግራለች።
ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
ከመግፋፋት በመውጣት የመደመር ዕሳቤን በማጎልበት በህዝቦች መካከል ያሉ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስክ ያስተማራቸውን 518 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል አለው – ሚ/ር ዴኤታ የትምጌታ አስራት