በትብብር ላይ የተመሰረተ ፉክክር በማጠናከር ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚገባ የሀዲያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ገለፀ
በዞኑ ሆሳዕና ከተማ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የዞኑ ልዩ ልዩ ስፖርት እና የባህል ስፖርት ሻምፕዮና ፍጻሜውን አግኝቷል።
በማጠቃለያ መርሃግብሩ ላይ የተገኙት የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መመሪያ ኃላፊ አቶ ታምሬ ኤርሚያስ፤ ስፖርታዊ ውድድሩ በትብብር ላይ የተመሰረተ ፉክክር በማጠናከር ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያለመ መሆኑን አንስተው ይህም በፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላ መልኩ እና በአንድነት መንፈስ መካሄዱን ተናግረዋል።
ተወዳዳሪዎች በአካላዊ እና በአዕምሮ ጎልብተው ያላቸውን አቅም እንዲያወጡ በማገዝ በተለያዩ ውድድሮች ዞኑን የሚወክሉና የሚያስጠሩ ተተኪዎች እንዲወጡ ዕድል የፈጠረ ስለመሆኑም አውስተዋል።
በመምሪያው የስፖርት ተሳትፎና ውድድር ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ መስፍን አበበ በበኩላቸው፤ በውድድሩ በዞኑ ካሉ 20 መዋቅሮች መካከል 6 ወረዳዎችና 4 ከተማ አስተዳደሮች በጠቅላላው 7 መቶ 44 ተወዳዳሪዎች በ14 የስፖርት ዓይነቶች መሳተፋቸውን ገልፀው በተሳትፎው ችሎታቸውን ያሳዩበት እንደሆነም አስረድተዋል።
በቀጣይ ወጥነት ባለው መልኩ በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ማካሄድ እንደሚገባ አስታውሰው፤ የስፖርት ቤተሰብ፣ መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለስፖርት ዕድገት በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
በማጠቃለያው በተካሄደው የወንዶች እግር ኳስ ጨዋታ የአምናው ሻምፕዮን ሆመቾ ከተማ አስተዳደር ከሻሾጎ ወረዳ ጋር ጨዋታ አድርጎ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በተከታታይ ዋንጫ ማንሳት ሲችል በሴቶች እግር ኳስ ደግሞ ሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።
በሌሎች ውድድሮች በአትሌቲክስ በወንዶች እና በሴቶች የምሻ ወረዳ የሜዳልያ አሸናፊ ሲሆን የሌሞ ወረዳ በስፖርታዊ ጨዋነት ተሸላሚ ሆኗል።
በባህላዊ የስፖርት ውድድር በሻህ፣ ቡም እና ገበጣ 12 ጉድጓድ ሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ማሸነፍ ሲችል፤ በገበጣ 18 ጉድጓድ ምስራቅ ባደዋቾ፣ በከርቦ ጊቤ ወረዳ፣ በከርቦ ድብልቅ ደግሞ የፎንቆ ከተማ አስተዳደር የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል።
በተደረገው ስፖርታዊ ወድድር 4 ዋንጫዎችን በማንሳት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ ውድድር አሸናፊ መሆን ችሏል።
በማጠቃለያው የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የየወረዳዎቹ የስፖርት ልዑካን እና የስፖርት ቤተሰብ በተገኙበት ፍጻሜውን አግኝቷል።
ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ከመግፋፋት በመውጣት የመደመር ዕሳቤን በማጎልበት በህዝቦች መካከል ያሉ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስክ ያስተማራቸውን 518 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል አለው – ሚ/ር ዴኤታ የትምጌታ አስራት