ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሳንባ ነቀርሳ በሽታ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መሥራት ወሳኝ ሚና እንዳለው የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
“በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ ማዕከል አቅምን በማጠናከር ሥር የሰደደ የመተንፈሻ አካላት በሽታ እና የሳንባ ነቀርሳን ድርብ ሸክም መፍታት” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላቭ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት የፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሃግብር አካሄዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በፌዴራል ጤና ሚኒስቴር የቲቢ ሥጋ ደዌ እና ሌሎች በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ አቶ ታዬ ለታ፥ የቲቢ በሽታ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው፥ የበሽታው አሳሳቢነትን በመረዳት የፌዴራል መንግሥት የምርመራ ሥራዎችን ማጠናከር እንዲሁም በበጀትና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን በመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
‘ላቭ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ’ በዘርፉ ላይ ፕሮጀክት ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራውን ለማሳለጥ አጋዥ አካላት በቅንጅት ከመሥራት ባሻገር የሚጀመሩ ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው መሥራት ይገባዋል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ የቲቢ በሽታ አሳሳቢነት እየተደረጉ ባሉ ምርመራዎች መረዳት መቻሉን ገልጸው፥ በዘርፉ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ተግባር ይጠበቃል ብለዋል።
የላቭ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አክሊሉ ሽሙሮ ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት በተለያዩ ዘርፎች ላይ እየሰራ መሆኑንና ከዚህ ልምድ በመውሰድ የሳንባ ነቀርሳ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ ታስቦ ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀዋል።
የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በምርምር ለማስደገፍ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የትብብር ም/ፕሬዝደንት ተወካይ እና የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ኃ/ማርያም ተናግረዋል።
በማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ ፕሮጀክቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 6 ዞኖች ተግባራዊ እንደሚሆን የተገለፀ ሲሆን ስለ ፕሮጀክቱ ዝርዝር ተግባራት ቀርቧል።
በመድረኩ ላይ የተገኙ ባለ ድርሻ አካላት ለፕሮጀክቱ ስኬት በቁርጠኝነትና በትብብር እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አማሮ አርሳባ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን
More Stories
ከመግፋፋት በመውጣት የመደመር ዕሳቤን በማጎልበት በህዝቦች መካከል ያሉ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስክ ያስተማራቸውን 518 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል አለው – ሚ/ር ዴኤታ የትምጌታ አስራት