የማህበረሰብን ተሳትፎ በማጠናከር የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ችግር በመፍታትና ልማትን በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስልጤ ዞን አስተዳደር ገለፀ

የማህበረሰብን ተሳትፎ በማጠናከር የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ችግር በመፍታትና ልማትን በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስልጤ ዞን አስተዳደር ገለፀ

በዞኑ ምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ በሪም የልማት ማህበር ከ42 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባ የሀዲያ ዞንን ከስልጤ ዞን የሚያገናኝ የመንገድና ተዛማጅ መሰረተ ልማቶች ምረቃና የባዛር ፕሮግራም ተካሂዷል።

በምረቃ መርኃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙበራ ከማል፤ የመንገድ መሰረተ ልማት የልማቶች ሁሉ መሰረት በመሆኑ የማህበረሰቡን የልማት እንቅስቃሴ ለማፋጠን፣ ለገጠርና ከተማ እድገት እንዲሁም ማህበራዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ወሳኝ በመሆኑ ለመንገድ ልማቱ እውን መሆን የአንበሳውን ድርሻ ለተወጡት የሪም የልማት ማህበር አባላት ምስጋናቸውን ቸረዋል።

በወረዳው የህብረተሰብ ተሳትፎ የተገኘውን ውጤት ወደ ሌሎች የልማት ዘርፎች በማስፋፋት የማህበረሰቡን ችግር የመፍታት እንቅስቃሴ መንግስት ይደግፋል ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው፤ በየጊዜው የሚሰሩ መሰረተ ልማቶችን መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከይረዲን ሀቢብ፤ የመንገድ መሰረተ ልማት ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ብሎም ማህበራዊ መስተጋብር ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።

በወረዳው በሪም ቀባሌ በከተማና በገጠር በሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች የተቋቋመው የሪም ልማት ማህበርና በአካባቢው ማህበረሰብ የ25 ኪሎ ሜትር የመንገድ ከፈታና ጥርጊያ፣ የድልድይ ግንባታን ጨምሮ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ የልማት ማህበሩ አባላት ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ዓላማ በማዋል በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችን በማስተባበር የህብረተሰቡን የልማት ችግር ለመቅረፍ እየሰሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ለመልካም ተግባራቸው መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ እውቅናን ይሰጣል ብለዋል።

አቶ ኑሪ ያሲን የሪም ልማት ማህበር አስተባባሪ ኮሚቴ አባል በበኩላቸው፤ ከአምስት ዓመታት በፊት ከአስር በማይበልጡ የአካባቢው ተወላጆች የተመሰረተው የሪም ልማት ማህበር በአካባቢው ያለውን የልማት ችግር ለመቅረፍ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች፣ ነጋዴዎችና ባለሀብቶችን በማስተባበር ከ42 ሚሊዮን ብር በለይ ወጪ 25 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ የመክፈት፣ የ04 ድልድዮች ግንባታ፣ 25 ኪሎ ሜትር ጠጠር የማልበስ፣ 4 ኪሎ ሜትር የነባር መንገድ ጥገና እና ሌሎችንም ስራዎች በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የልማት ማህበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ እውን ለማድረግ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ለመስራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ያሉት አስተባባሪው፤ የአካባቢውን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው የመንገድ መሰረተ ልማት ከዚህ ቀደም ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት የሚያስቀርላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በማህበሩ የተገነቡ ድልድዮችና የመንገድ ስራዎች ምረቃ ጎን ለጎን የመብራት ገቢ አሰባሰብ ባዛር የተካሄዳ ሲሆን በዚህም ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የዞንና የወረዳው ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ የሪም ልማት ማህበር አባላትና የአጎራባች አካባቢ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: ሙጂብ ጁሃር – ከሆሳዕና ጣቢያችን