የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በበጋ መስኖ የተለያዩ አትክልትና አዝርእት በዘር መሸፈኑን የአሪ ዞን የባኮዳውላ አሪ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ገለጸ

የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በበጋ መስኖ የተለያዩ አትክልትና አዝርእት በዘር መሸፈኑን የአሪ ዞን የባኮዳውላ አሪ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 03/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በበጋ መስኖ በ1ኛና 2ኛ ዙር ከ 1ሺህ 470 ሔክታር መሬት በአትክልትና አዝርእት በዘር መሸፈኑን በአሪ ዞን የባኮዳውላ አሪ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ገለጸ።

ዝናብን ብቻ ከመጠበቅ ተላቀው በመስኖ ማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የወረዳው አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

የባኮ ዳውላ አሪ ወረዳ በበጋ መስኖ ከሚያለሙ ወረዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን፥ በዘንድሮ የበጋ መስኖ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በ12 ቀበሌዎች በ1ኛና 2ኛ ዙር ከ1ሺ 900 ሔክታር በላይ መሬት በተለያዩ የጓሮ አትክልትና አዝርእት ለማልማት ታቅዶ ከ1ሺ 470 ሔክታር በላይ መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ምክትል ሀላፊና የእርሻ ዘርፍ ሀላፊ አቶ በረከት ወንድሙ ተናግረዋል።

በአከባቢው ቀድሞ በስፋት ከሚለሙ ሽንኩርት፣ ቀይስር፣ ስንዴ እና ቦሎቄ በተጨማሪ ዘንድሮ በአዲስ መልክ ቲማቲምና ቃርያ የማልማት ስራ የተጀመረ ሲሆን፥ አርሶ አደሩም ተሞክሮውን በማየት በቀጣይ በስፋት በማምረት ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎቱ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።

ያመረቱትን ምርት ወደ ተሻለ የገበያ አማራጭ በማቅረብ በተሻለ ዋጋ መሸጥ እንዲችሉ የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በረከት፥ በበጋ መስኖ ተግባር በወረዳው ከ10ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተሳታፊ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለመስኖ ተግባር የሚውሉ ከ 70 በላይ የውሃ መሳብያ ጀነሬተሮች አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነና በምርት ዘመኑ ማጠቃለያ በ1ኛና 2ኛ ዙር ከለማው ከ283 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ጌታቸው ናቸው።

በእርሻ ማሳቸው ለይ እንክብካቤ እያደረጉ ያነጋገርናቸው አርሶ አደር አለማየሁ አንግሲ እና አርሶአደር አስናቀ ባይስማል እንደተናገሩት በዘንድሮው የበጋ መስኖ ቃርያ ቲማቲም እና ስንዴ እያለሙ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ባለፈው ባመረቱት ምርት የቤተሰባቸውን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፈው በተሻለ ዋጋ በመሸጥ የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ ችለዋል።

ዝናብን ብቻ ከመጠበቅ የውሃ አማራጮችን ተጠቅመው በመስኖ በአመት ሁለቴና ከዛ በላይ አልምተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን ሰይፉ – ከጂንካ ጣቢያችን