በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በጤና መድህን አገልግሎት ከብዙ ወጪ እየተረፉ መሆናቸውን ተናገሩ

የ2017 ዓ.ም የጤና መድህን መዋጮውም በወረዳው የህብረተሰቡን የገቢ አቅም ያገናዘበ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሎማ ቦሣ ወረዳ ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው አቶ ዋሴ በተላ፣ ወ/ሮ ታደለች ፈለቀ፣ አቶ አማኑኤል ደጋታና እና ሌሎችም በሰጡት አስተያየት የጤና መድህን አገልግሎት በመጠቀማችን ዘርፈ ብዙ ጥቅም አግኝተናል ብለዋል።

በታመምን ቁጥር ከፍለን መታከም ለማንችለው ዝቅተኛ ገቢ ላለን በተለይም ጠቅሞናል ሲሉ ተናግረዋል።

አካባቢያችን በአብዛኛው ቆላማ የአየር ፀባይ ያለው እንደመሆኑ ለአብነትም ለወባ በሽታና በመሰል ሌሎች በሽታዎች በተደጋጋሚ አንደመጋለጣችን የጤና መድህን ባይኖርና የአገልግሎቱም ተጠቃሚ ባንሆን ኖሮ ወጪውን አንችለውም ነበር ብለዋል።

በተጨማሪም የመድኃኒት ዋጋ እንደሃገር እየናረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት በዓመት አንድ ጊዜ ለዚያውም በትንሽ ገንዘብ ከጤና ጣቢያ እስከ ከፍተኛ ሆስፒታል ድረስ የምንታከመበትን ይህንን ዕድል መንግስት በማመቻቸቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በ2017 ዓ.ም ያለው የጤና መድህን መዋጮ ገንዘብ ትንሽ ጭማሪ ያደረገ ቢሆንም በወቅቱ ካለው የመድሐኒት ውድነት ጋር ሲነጻጸር አሁንም ጥቅሙ ለእኛው ነው ብለው ነገር ግን አልፎ አልፎ የሚታየው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እንዲሻሻል ጠይቀዋል።

በወረዳው ካሉ የጤና ተቋማት መካከል የያሎ ጤና ጣቢያ ኃላፊ ተወካይ የሆኑት ሀኪም አድማሱ አማሞ፤ እንደ ጤና ጣቢያቸው ያሉትን የማጤማ ተገልጋዮችን በተገቢው እንደሚያስተናግዷቸው ገልፀዋል።

ከመድኃኒት አቅርቦቱ ጋር በተያያዘ ግን አልፎ አልፎ የወባና መስል በሽታዎች በአካባቢው እየተስፋፉ በመሆናቸው መድኃኒቶቹ ቶሎ እንደሚያልቁ ተናግረዋል።

የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ዶግሶ በሰጡት አስተያየት፤ በወረዳው ባሉ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች የተፈጠረው የመድኃኒት እጥረት እንደአጠቃላይ ጊዜያዊ የነበረ መሆኑን ገልጸው ችግሩ የተፈጠረው አልፎ አልፎ የማጤማ ተጠቃሚዎች የነፍሰ-ወከፍ ክፍያ የመዋጮ ገንዘባቸውን በወቅቱ ገቢ ባለማድረጋቸው እንደነበር አውስተዋል።

ችግሩም አሁን የተቀረፈ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በ2017 ዓ.ም ካለው የማጤማ መዋጮ ጋር በተያያዘም ሃላፊው ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ የገንዘብ ጭማሪ መኖሩን በማንሳት ይኸውም እንደሃገር በዘርፉ የተጠናውን ጥናት መነሻ በማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን