ስፖርት አንድነትን በማጠናከር ሰላምን ከማስፈን ባለፈ ለሀገር እድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለፀ

“ስፖርታዊ ልማት ለአሸናፊ ሀገር” በሚል ሁለተኛው መላ የአሪ ዞን ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ሻምፒዮናና የባህል ስፖርቶች ውድድር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በውድድሩ ህገ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የአሪ ዞን ወጣቶችና ሰፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ይኸነው ተስፋዬ ፤ ስፖርት አንድነትን በማጠናከር ሰላምን ከማስፈን ባለፈ ለሀገር እድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልፀው የአሪ ዞን ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም በስፖርቱ ዘርፍ እያስመዘገበ ያለውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል ከዚህ ቀደም በነበሩ ስፖርታዊ ውድድሮች የታዩ ደካማ ጎኖችን ማረም አስፈላጊ በመሆኑ በህገ ደንቡ ዙሪያ ውይይት ማድረግ ማስፈለጉን ተናግረዋል።

ከየካቲት 2 እስከ 9/2017 ዓ.ም በሴቶችና በወንዶች እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ፓራኦሎንፒክ፣ ወርልድ ቴኳንዶን ጨምሮ ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ገልፀው፤ የዘንድሮውን ውድድር ለየት የሚያደርገው 3 የባህላዊ ስፖርት አይነቶች ውድድር መካሄዳቸው ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ዞኑን በመወከል በክልል፣ በሀገር ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚካሄደው የስፖርት ሻምፒዮና ውድድር ስፖርታዊ ጨዋነት በመላበስ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት በሃላፊነት መወጣት እንደአለባቸው አመላክተዋል።

የውድድሩ ህገ ደንብ ሰነድ በዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የተሳትፎና ውድድር ቡድን መሪ አቶ አየናቸው ጥላሁን ቀርቦ የጋራ ውይይት ተደርጎበታል ።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች የቴክኒክ ኮሚቴ የተጫዋች ተገቢነት ምልመላ፣ የዳኛና የመስመር ዳኛ አለመናበብ ፣ አግባብ ያልሆነ የካርድ እና የተጨማሪ ሰዓት አሳጣጥ እንዲሁም በአሰልጣኞች ቡድን መሪዎች እና ኮቾች ዙሪያ የሚስተዋል ስሜታዊነት እና የሴቶች ተሳትፍ ዝቅተኛ መሆን ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

የአሪ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ማታዶ በርቢ፤ የጂንካ ከተማ የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር መቀመጫ በመሆኗ እና ትምህርት የተዘጋበት ወቅት በመሆኑ በርካታ ታዳሚዎች ስለሚገኙ ውድድሩ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ስፖርተኞች፣ ደጋፊዎች እና ሌሎች የውድድሩ ባለድርሻ አካላት ውድድሩን ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መንገድ ማካሄድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን