የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ደን ሃብቶችን በመንከባከብና በማልማት የተፈጥሮ ስርዓተ-ምህዳር ሚዛን ሳይዛባ ለትውልድ ለማቆየት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ደን ሃብቶችን በመንከባከብና በማልማት የተፈጥሮ ስርዓተ-ምህዳር ሚዛን ሳይዛባ ለትውልድ ለማቆየት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፉት 6 ወራት የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራትን የገመገመ ሲሆን፥ የአከባቢ ብክለት በሚፈፅሙ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥር እና ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
የክልሉ የደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ በበኩላቸው በአለማችን እየተከሰተ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥን አደጋ ተቋቁመን ለትውልድ የሚተርፍ የአካባቢ ጥበቃ ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።
የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ደን ሃብቶችን በመንከባከብና በማልማት የተፈጥሮ ስርዓተ-ምህዳር ሚዛን ሳይዛባ ለትውልድ ከማቆየት ባሻገር፥ የደን ሽፋን በማሳደግ ዘርፉ ለክልሉ ብሎም ለሀገር እኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
ህጋዊ ደረሰኝ ሳይኖራቸዉ በህገወጥ መንገድ የደን ሀብት ሲያዘዋዉሩ በተገኙ ግለሰቦች ላይ እርምጃ በመውሰድ 433.5 ሜትር ኪዩብ የደን ሀብት መውረስ መቻሉ ተመላክቷል።
የክልሉ ደን ሽፋን ለማሳደግ በአዲሱ በጀት ዓመት ከ243.9 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በማዘጋጀት ከ208.4 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውና ዓላማን መሠረት ያደረጉ ችግኞችን በመትከል አሁን ያለዉን የደን ሽፋን ከ23.17% ወደ 23.87% ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ለግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው ሪፖርት አመላክቷል።
የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ በዘርፉ የተከናወኑ ጠንካራ አፈጻጸሞች የበለጠ ሊሰፋና በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመው፥ በግማሽ ዓመቱ የተስተዋሉ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል እና ድክመቶችን በማረም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተያያዘ ዜና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህል ቱሪዝም ቢሮ በ2017 የመጀመሪያ ግማሽ በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርቱን ለግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።
በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ተብሏል።
በዩኔስኮ የተመዘገቡ የኮንሶና ጌዴኦ መልክአ ምድር አለም አቀፍ ቅርሶች አጠባበቅ አዋጅ መጽደቁን ተከትሎ ለአፈጻጸም የሚረዳ ማስፈፀሚያ ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱ ለዘርፉ ጥበቃ ዘላቂነት የተሰጠዉን ትኩረት እንደሚያሳይ ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል።
የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳደር ጽ/ቤት ለማደራጀት የተያዘዉ እቅድ እስካሁን ተግባራዊ መሆን ያለመቻል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመልክቷል።
ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
ከመግፋፋት በመውጣት የመደመር ዕሳቤን በማጎልበት በህዝቦች መካከል ያሉ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስክ ያስተማራቸውን 518 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል አለው – ሚ/ር ዴኤታ የትምጌታ አስራት