ጊዜ ያለፈባቸው የተለያዩ መድኀኒቶችን ለህክምና አገልግሎት ሲያውሉ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን በዳውሮ ዞን የሎማ ቦሣ ወረዳ ፓሊስ አስታወቀ
መድኃኒቶቹ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው በመሆኑ የተጠቀሙት ሰዎችም ታመው በህክምና ላይ እንደሚገኙ ነው የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት እንዲሁ የገለፀው፡፡
በዳውሮ ዞን የሎማ ቦሣ ወረዳ ፓሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ኢንስፔክተር አብረሃም አቱሞ እንደገለፁት፤ በወረዳው ህገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
በቅርቡ በወረዳው ህጋዊ የህክምና ፍቃድ ሳይኖራቸው የህክምና አገልግሎት ሲሰጡና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የሆኑ መድኃኒቶችን በማስገባት ሲገለገሉና ሲያስገለግሉ የነበሩትን ግለሰቦች ፖሊስ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር ግብረ ሀይል በማቋቋም እጅ ከፍንጅ በመያዝ በቁጥጥር ስር አውሏል ብለዋል።
እነዚህን መሰል ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚጎዱ ሌሎችም ካሉና የሚገኙም ከሆነ ለህግ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደውን ትብብር ህብረተሰቡ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በወረዳው ፓሊስ ጽህፈት ቤት የምርመራ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ሻለቃ ጌታቸው በካሎ በበኩላቸው፤ በህገወጥ ተግባር የተሰማሩት በርካታ ግለሰቦች በወረዳው መኖራቸውን የደረሰን ጥቆማ ፍንጭ በመስጠቱ ይህን ተከትሎም ከፍርድ ቤት በተሰጠን የብርበራ መብት ተጠርጣሪዎችን ከነመድኃኒቶቹ በመያዝ ለህግ ማቅረብ ችለናል ሲሉ ተናግረዋል።
የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ብረሃኑ ዶግሶ በሰጡት አስተያየት፤ በኮንትሮባንድ መልክ ወደ መድኃኒት ንግድ አንዳንድ ግለሰቦች በወረዳው መሰማራታቸውንና ከነዚህም መካከል ስነ-ምግባር የጎደላቸው የጤና ባለሙያዎች ጭምር የሚገኙበት መሆኑን አንስተው አሁን ግን ድርጊታቸው ተደርሶበት ጉዳዩ በህግ ቁጥጥር ስር በመሆን እየተጣራ ይገኛል ብለዋል።
የሎማ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ ዘለቀ ሲሳይ በበኩላቸው፤ በወረዳቸው የወባ በሽታ ህብረተሰቡን በስፋት እያጠቃ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ተከትሎም እኩይ ባህርይን የተላበሱ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶ አደሮች እና ሌሎችም የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈባቸውን መድኃኒቶች ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ወረዳው በማስገባት ሲሸጡ እንደነበርና ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ : አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
ከመግፋፋት በመውጣት የመደመር ዕሳቤን በማጎልበት በህዝቦች መካከል ያሉ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስክ ያስተማራቸውን 518 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል አለው – ሚ/ር ዴኤታ የትምጌታ አስራት