መደበኛ ያልሆኑ የሰዎች ዝውውሮችና  ከአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ በትኩረት መስራትን እንደሚጠይቅ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሴቶች ፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ

መደበኛ ያልሆኑ የሰዎች ዝውውሮችና  ከአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ በትኩረት መስራትን እንደሚጠይቅ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሴቶች ፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮን የግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀም ገምግሟል።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ በማህበራዊ ዘርፍ በርካታ ስራዎች መተግበራቸውንና የተሻሉ አፈፃፀሞች መኖሩን የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በሪፖርቱ አስታውቋል።

በ2017 የግማሽ በጀት ዓመት የህፃናትን ፍልሰት እና ጎዳና ተዳዳሪነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውንና በማህበራዊ ጥበቃ ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች በተሻለ ደረጃ መፈፀማቸውንም ቢሮው አስታውቋል።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ስምሪት ላይ በክልሉ በተከናወኑ ተግባራት የተሻሉ አፈፃፀሞች መኖራቸውም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የአካል ጉዳተኞች የአካቶ ተግባር፣የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገርራት ሥራ ስምሪት ጋር በቀጣይ ትኩረት የሚያሻቸው መሆኑንም ተገልጿል።

እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እመቤት ወንድሙ ገለፃ ቢሮው ከህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመከላከል፣የሙያ ደህንነትን ለማረጋገጥ ፣ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ቢሮው የሰራቸው ተግባራት የተሻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከአሰሪና ሰራተኞች አደረጃጀት፣ከስራ ቦታዎች ቁጥጥር፣መደበኛ ካልሆኑ የሰዎች ዝውውርና ከአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ ተግባራት ትኩረትን እንደሚሹ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተናግረዋል።

እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዋኖ ዋሎሌ (ዶ/ር) መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከል በተሰሩ ስራዎች ተጠያቂነት የማስፈን ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው ከአካል ጉዳተኞች እንዲሁም ከጎዳና እና ከሴተኛ አዳሪዎች ተጠቃሚነትና ማደራጀት ጋር ተያይዞ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።

በግማሽ ዓመቱ የስራ አፈፃፀም ግምገማም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እመቤት ወንድሙን ጨምሮ የቋሚ ኮሚቴው አባላት እንዲሁም  የቢሮ ኃላፊና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: ቃለአብ ጸጋዬ