የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት ለሶሰት ወራት ያሰለጠናቸውን 102 የህግ ባለሙያዎችን አስመረቀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት ለሶሰት ወራት ያሰለጠናቸውን 102 የህግ ባለሙያዎችን አስመረቀ

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ፤ ስልጠናው ለዳኝነትና ለፍትህ አካላት ቀጣይነት ያለውና ጥራቱን የጠበቀ ስልጠና መስጠት ለህዝቡ ፈጣንና ቀልጣፋ ፍትህ ለመስጠት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበትና ፍትህ የሰፈነበትን ክልል የመገንባት ራዕይ እውን እንዲሆን ተመራቂዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለበቻው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የኢፌዲሪ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የዘርፍ እንባ ጠባቂ አቶ አባይነህ አዴቶ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ፍትህ ተቋማት ላይ በአሰራር፣ በአደረጃጀትና በህግ ማዕቀፎች ዙሪያ የህግ ጥናትና ምርምር እያደረገ ለፍትህ ስርዓቱ መሻሻል የራሱን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ህዝቡ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ሚዛናዊ ፍትህ እንዲያገኝ የፍትህ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩና የህግ ባለሙያዎች ብቃታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ይበልጥ ለማጎልበት በኢንስቲትዩቱ እየተሰራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ተወካይና የስልጠና ማማከር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ግርማሼ፤ ኢንስቲትዩቱ ለሶስት ወራት ባዘጋጀው የስልጠና መርሃ-ግብር ከተሳተፉ 102 ዳኞች፣ ዓቃቤያነ ህጎችና ረዳት ዳኞች መካከል ሰባቱ ሴቶች መሆናቸውን በምረቃው ስነ-ስርዓት ገልጸዋል፡፡

ከ12ቱ ዞኖች የተወጣጡ ዳኞች፣ ረዳት ዳኞችና ዐቃቢያነ ህጎች በ18 የተየያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የህግ ኮርሶችን ተከታትለው በማጠናቀቅ ለምረቃ መብቃታቸውን አቶ ጌታሁን አብራርተዋል።

የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ መሰረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ወሰነ በመልዕክታቸው፤ ህዝቡ የሚፈልገውን ፈጣን ቀልጣፋና ሚዛናዊ ፍትህ ያገኝ ዘንድ ተመራቂዎች የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አሳስበዋል፡

ካነጋገርናቸው ተመራቂ ባለሙያዎች መካከል አቶ ይርጋለም ረታ፣ አቶ አሸብር ነቃ እና ወ/ሮ የምስራች ጥላሁን በሰጡት አስተያየት ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት ህብረተሰቡን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን