የአደንዛዥ ዕጾች በዜጎች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እየጨመረ በመሆኑ ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን ሀላፊነት እንዲወጣ ተጠየቀ

የማዕከላዊ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት የአደንዛዥ ዕጽ በዜጎች ላይ በሚያሰከትለው ጉዳት ዙሪያ ያካሔዱት ምርምር ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ ውይይት ተካህዶበታል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ አቶ ሎምባ ደምሴ እንዳሉት የተለያዩ አደንዛዥ ዕጾችን መጠቀምና ተገዢ መሆን ለማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና አካላዊ ጉዳት ከመዳረጉም በላይ ራስን እስከማጥፋት እያደሰ እንደምገኝ ገልጸው በማወቅም ሆነ ባለማውቅ በተግባሩ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመታደግ ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም ሀላፊነቱን ካልተወጣ የአሳሳቢነቱ መጠን እየጨመረ ነው።

ንቁ እና አምራች ሀይል እየጎዳ ያለውን የአደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚነትን ለመቀነስ  መንግሥት የተለያዩ ተግባራትን እያከሔደ ቢሆንም በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  ሠራተኛ እና ማህበራዊ  ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ዋኖ ዋሉሌ ዶ/ር  ናቸው።

በሁለቱ ክልሎች ከሚገኙ ስድስት ዋና ዋና ከተሞች የተወሰደው ናሙና እንደሚያመለክተው የአደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚነት እና የተጎጂዎች መጠን እየጨመረ ከመምጣቱም በላይ ከማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና  ለሕይት መጥፋት መንስኤ ስለመሆኑም ተብራርቷል።

የችግሩን አሳሳቢነት በአግባቡ በመረዳት ቤተሰብ ከልጆች አስተዳደግ እና አያያዝ ጀምሮ የትምህርት ተቋማት እና ባለ ድርሻ አካላት ለስብዕና ግንባታ በትኩረት እንዲሠሩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጠይቀዋል።

በውይይት መድረኩ የሁለቱም ክልሎች የሥራ ሀላፊዎች እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ተገኝተውበታል።

ዘጋቢ ወ/ገብርኤል ላቀው ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን