ከተሞች የውስጥ አቅማቸውን በማሳደግ ከሌሎች አቻ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተሰራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ

ከተሞች የውስጥ አቅማቸውን በማሳደግ ከሌሎች አቻ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተሰራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ

በጎፋ ዞን በመዋቅራዊ ፕላን ማሻሻያ ወደ ሣውላ ከተማ የተካለሉ ቀበሌያትን በተመለከተ በደንባ ጎፋ ወረዳና በሣውላ ከተማ አስተዳደር አመራሮች መካከል የክልልና የዞን አመራሮች በተገኙበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ቱርቃቶ ቱርቶ ሣውላ ከተማ በክልሉ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፈጣን ዕድገት ላይ የምትገኝ ከተማ መሆኗን ጠቅሰው፤ ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ማስተሳሰርና ሀብት በማፍራት የሚመጥናትን ዕድገት ማምጣት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ከተማዋ የተካለሉ ቀበሌያትን ታሳቢ ያደረገ የመሰረተ ልማት ግንባታ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ዶክተር ቱርቃቶ አሳስበዋል።

በክልሉ ከተማ ልማትና መሠረተ ልማት ቢሮ የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳምነው አዲሱ በበኩላቸው፤ ከተሞች የውስጥ አቅማቸውን በማሳደግ ከሌሎች አቻ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተሰራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አስረድተዋል።

ፕላን ለከተሞች ዕድገት ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ ትግበራው በውጤታማነት እንዲፈጸም የነዋሪው ድርሻ የላቀ መሆኑን አቶ አሳምነው ገልጸዋል።

የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ወሰኔ እንደገለፁት፤ በአዲሱ የከተማው ፕላን መሰረት በመሉ አቅም ወደ ስራ በመግባት የከተማውን ዕድገትና ብልጽግና በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል።

የሣውላ ከተማ ዕድገት ለሌሎች አጎራባች ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ለተግባሩ ስኬታማነት ቁርጠኛ መሆናቸውን የከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ጳውሎስና የከተማው ከንቲባ አቶ እርቦላ እርኮ ገልጸዋል።

የጋራ የሆነችውን ከተማ ለማልማት አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር በማድረግ ለዕድገቷ መፋጠን የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የደንባ ጎፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ አራታ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ወደ ከተማዋ ከተካተቱ ሠዝጋ፣ የላ፣ ጉራዴና ሱካ ቀበሌያት በተጨማሪ የፃንባ ፃላና ቱርጋ ቀበሌያት ከደንባ ጎፋ ወረዳ ወደ ሣውላ ከተማ የተካለሉ መሆናቸው ተገልጿል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ከተማዋን ከማልማት አኳያ ተቀናጅቶና ተደጋግፎ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን