በደም አቅርቦትና ፍላጎት ላይ የሚታየውን ክፍተት በመሸፈን በደም እጦት የሚጠፋውን ህይወት መታደግ እንደሚገባ ተጠቆመ

በደም አቅርቦትና ፍላጎት ላይ የሚታየውን ክፍተት በመሸፈን በደም እጦት የሚጠፋውን ህይወት መታደግ እንደሚገባ ተጠቆመ

የሚተካ ደም በመለገስ የማይተካ ህይወትን ለመታደግ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የአርባምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አስታውቋል።

የኮሌጁ መምህራን፣ ተማሪዎችና ሰራተኞች በፍቃደኝነት ደም ለግሰዋል።

ተማሪ ረዲኤት ሚልኪያስና በቃልኪዳን ይርጉ የአርባምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ በአደጋና ወሊድ ምክንያት የሚጠፋውን ህይወት ለመታደግ በማሰብ ደም መለገሳቸውን ጠቁመዋል።

በመለገሳቸው ተጠቃሚ መሆናቸውንም በመግለፅ።

በአርባምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የደም ባንክ አስተባባሪ አቶ ኤርሚያስ መኩሪያ፤ በየአመቱ የኮሌጁ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የማህበረሰብ አካላት ደም እየለገሱ መቆየታቸውን አውስተው በዚህም የበርካታ ወገኖችን ህይወት መታደግ መቻሉን አብራርተዋል።

በአርባምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ካሳሁን ታመነ፤ ኮሌጁ ከመማር ማስተማርና ምርምር አገልግሎት ባሻገር በማህበረሰብ አገልግሎት ማህበረሰብ ተኮር ተግባራትን እያከናወነ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በደም እጦት ምክንያት በርካታ የማህበረሰብ አካላት ህይወታቸውን እንደሚያጡ የጠቆሙት አቶ ካሳሁን፤ መርሀ ግብሩ በቋሚነት እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የአርባምንጭ ደም ባንክ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታገል ጌታቸው፤ አገልግሎቱ በአመት 9 ሺህ ዩኒት ደም ለመሠብሰብ ማቀዱንና በኮሌጁ ከሚለገሰው ደምም 180 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልፀዋል።

ደም በተፈጥሮ በሰውነታችን የሚመረት ንጥረ ነገር ነው ያሉት አቶ ታገል፤ አንድን ሰው ከህመምና ስቃይ እንዲሁም ከሞት ለመታደግ ደም የመለገስ ባህላችንን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን