የቤንች ማጂ ልማት ማህበር በመንግስት ተደራሽ ያልሆኑ ተግባራትን ከማከናወኑም ባለፈ በማህበራዊ ዘርፍ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አስታወቀ
ልማት ማህበሩ የራሱ ቢሮ እና ገቢ እንዲኖረውም እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የቤንች ማጂ ልማት ማህበር ባለፉት 27 ዓመታት ከ171 በላይ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደረጉ ተግባራትን ሲያከናወን መቆየቱን የልማት ማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ አፅናኝ ፈለቀ ተናግረዋል።
ልማት ማህበሩ በ 4 ዘርፎች በአባላት ማፍራት፣ በፕሮጀክት፣ በፋይናንስና በአስተዳደር ዘርፎች ዋና ዋና ተግባራትን ለይቶ ከመስራቱም ባለፈ በጤና በትምህርት የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።
ልማት ማህበሩ በመንግስት ተደራሽ ያልሆኑ ልማቶችን እያከናወነ በመሆኑ በቀጣይም ማህበሩን ሊያሻገሩ የሚችሉ ውሳኔዎች በቅርቡ በተደረገው ጉባኤ እንዲተላለፉ መደረጉን አቶ አፅናኝ ተናግረዋል።
በዚህም 463 ካሬ ሜትር ቦታ ለቢሮ፣ 4 ነጥብ 1 ሄክታር መሬት ቦታ ለባለ ልዩ ተስጥኦ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ በሚዛን አማን ከተማ ከማስቀመጣቸውም ባለፈ በጉራፈርዳ ወረዳ 200 ሄክታር ቦታ ለእርሻ የሚሆን ማሳ ርክክብ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።
ለአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመማሪያ ክፍል ዕጥረትን ለመቅረፍ በሚደረገው ርብርብ 8 ክፍሎችን የያዘ ባለአንድ ፎቅ ህንፃ ለመገንባት ቃል መገባቱንም ስራ አስኪያጁ አሰረድተዋል።
ልማት ማህበሩ 4 ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ወደ ረጂ ድርጅቶች ልኮ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ አፅናኝ፤ አቅም ለሌላቸውና የመማር ዕድል ለማያገኙ 340 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም አብራርተዋል።
ተቋሙ ከወባ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የመድኃኒት ችግሮችን ለመቅረፍ የማህበረሰብ አቀፍ መድኃኒት መድብር ለመክፈት ማቀዱን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
በተለይም ተቋሙን ወደፊት ሊያሻገሩ የሚችሉ በሀብት አሰባሰብ፣ በአባላት ማፍራት እንዲሁም በመማር ማስተማር ስራ ዘርፍ የግብዓት ዕጥረቶችን በመቅረፍ ረገድ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አቶ አፅናኝ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከሚዛን ዕድገት ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ካነጋገርናቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ስጦታ ግርማ፣ ተማሪ ፍቅርተ ጃሹና ተማሪ አማኑኤል አድማሱ በሰጡት አስተያየት የላብራቶሪ ግብዓት አለመሟላቱ በንድፍ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር እንዳያረጋግጡ እንቅፋት በመሆኑ ት/ቤት እና ልማት ማህበሩ ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት ችግሩን እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።
የሚዛን ዕድገት ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር ዝናው ታደሰ በበኩላቸው፤ 3ቱም ቤተ ሙከራዎችን የፊዚክስ፣ የኬሚስትሪና የባዮሎጂ ክፍሎችን በዲጂታል ለማደራጀት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ በመደበኛነት ከሚያስተምራቸው መካከል 12 ተማሪዎችን በመለየት ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት በተሻለ መልኩ ሊያስመዘግብ የሚችሉትን እየደገፈ እንደሚገኝ ርዕሰ መምህሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
ከመግፋፋት በመውጣት የመደመር ዕሳቤን በማጎልበት በህዝቦች መካከል ያሉ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስክ ያስተማራቸውን 518 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል አለው – ሚ/ር ዴኤታ የትምጌታ አስራት