አዋሽ ባንክ ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታትና ለመደገፍ የሚያካሂደው የ”ታታሪዎቹ” ውድድር የማህበራዊ ሀላፊነቱ ብራንድ አድርጎ ለማስቀጠል አልሞ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዋሽ ባንክ ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታትና ለመደገፍ የሚያካሂደው የ”ታታሪዎቹ” ውድድር የማህበራዊ ሀላፊነቱ ብራንድ አድርጎ ለማስቀጠል አልሞ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ባንኩ ለሁለተኛው ምዕራፍ የ”ታታሪዎቹ” ውድድር አሸናፊዎች ሽልማት አበርክቷል።

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ባዘጋጀው የሁለተኛው ምዕራፍ የ”ታታሪዎቹ” የሥራ ፈጠራ ውድድር ማጠቃለያ መርሀ ግብር ላይ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው እንደተናገሩት፤ ባንኩ የ”ታታሪዎቹ” የሥራ ፈጠራ ውድድር ከተጀመረበት ከ2015 ዓም ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ሲያከናውን ቆይቷል።

ባንኩ ለመጀመሪያው ምዕራፍ ውድድር አሸናፊዎች በፈጠረላቸው ዕድል አበረታች ስኬቶች ለማየት መቻሉንም አቶ ፀሀይ ገልፀዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ለመወዳደር ከሁሉም ክልሎች፣ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 5000 ያህል አዳዲስና ችግር ፈቺ የሥራ ሀሳብ ያላቸው ተሳታፊዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ብቃት ባላቸው ዳኞች ተለይተው ወደ ሁለተኛ ዙር የተሸጋገሩት 1688 ተወዳዳሪዎች በ30 የሥልጠና ማዕከላት ተደልድለው በ10 የብሔረሰብ ቋንቋዎች የክህሎት ሥልጠና የተሰጣቸው መሆኑን አቶ ፀሀይ ተናግረዋል።

እንዲሁም እንደ አቶ ፀሀይ ገለፃ፤ በሁለተኛው ዙር ከተወዳዳሪዎች መካከል በተደረገው ብርቱ ፉክክር በውጤታማነት የተለዩት 20 ተወዳዳሪዎች ወደ ሦስተኛው ዙር ተሸጋግረው የሥራ ሀሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችላቸው ተጨማሪ ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።

ባንኩ በዚሁ በሁለተኛው ምዕራፍ የ”ታታሪዎቹ” የሥራ ፈጠራ ውድድር ከ1ኛ ደረጃ እስከ 5ኛ ደረጃ በአሸናፊነት ለተወጡት ከብር 200,000 እስከ ብር 1,000,000 ሽልማት ያበረከተላቸው ሲሆን በውድድሩ ከ6ኛ እስከ 12ኛ ደረጃ ላገኙት አሸናፊዎቸ ከብር 40,000 እስከ ብር 100,000 ሸልሟቸዋል።

በተለይም በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ደረጃ ላገኙት አሽናፊዎች ከተሰጣቸው ሽልማት በተጨማሪ የሥራ ሀሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችላቸው አስከ ብር 5,000,000 ከዋስትና ነፃ የሆነ ብድር እንደሚመቻችላቸው የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፀሀይ በሽልማት ሥነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር አስረድተዋል።

“ታታሪዎቹ” በሚል መጠሪያ የሚካሄደው የአዋሽ ባንክ የሥራ ፈጠራ ውድድር የተቀረፀበት መንገድ በአሸናፊነት የተሸለሙት ብቻ ሳይሆኑ በውድድሩ የተሳተፉት ሁሉ ዘላቂ የሆነ ጠቀሜታ በማግኘት መሠረታዊ የንድፈሀሳብ አዘገጃጀት የቢዝነስ ፕላን አቀራረፅና የተግባቦት ክህሎት የመሳሰሉትን ዕውቀቶች የሚቀስሙበት ሥልጠና እንዲሆን ማስቻሉ የውድድሩ ትልቁ ስኬት መሆኑን በመገንዘብ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አቶ ፀሀይ አሳስበዋል።

በመጨረሻም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ፀሀይ የሥራ ፈላጊዎች ዋና ዋና እንቅፋቶች የሆኑትን የክህሎት የሥራ መነሻ ካፒታልና ሥራ ከተጀመረ በኋላ የሚያስፈልገውን የሥራ ማስኬጃ እጥረት በመቅረፍ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማ ያለው የ”ታታሪዎቹ” የሥራ ፈጠራ ውድድር የአዋሽ ባንክ የማህበራዊ ሀላፊነት ብራንድ አድርጎ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የ”ታታሪዎቹ” የሥራ ፈጠራ ውድድር ማጠቃለያ ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ በበኩላቸው፤ አዋሽ ባንክ የሚያካሂደው የሥራ ፈጠራ ውድድር የወደፊቱ ባለሀብት ኢትዮጵያውያን የመፍጠር ሥራ መሆኑን በአድናቆት ገልፀው ይህ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ ይሰጣል ብለዋል።

ዶክተር ተሻለ አክለውም ሁሉም ባንኮች አርአያነቱን ተከትለው ተመሳሳይ ሥራ ውስጥ እንደሚገቡ ያላቸውን ተስፋ ገልዋል።

ተሸላሚዎች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ባንኩ የሰጣቸው ሥልጠና የሥራ ፈጠራና የቢዝነስ ፕላን ቀረፃ ችሎታቸውን ለማጎልበት የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ንጋቱ ወልዴ