2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን በገቢዎች ሚኒስቴር የሀዋሳ ቅርጫፍ ፅ/ቤ አስታወቀ

2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን በገቢዎች ሚኒስቴር የሀዋሳ ቅርጫፍ ፅ/ቤ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ጥር 24/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት ስድስት ወራት 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን በገቢዎች ሚንስቴር የሀዋሳ ቅርጫፍ ፅ/ቤት አስታውቋል፡፡

የቅርንጫ ፅ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ታደሰ ለደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት እንደገለፁት፥ የግማሽ አመቱን ዕቅድ 95 በመቶ ማሳካት መቻሉን አመልክተው መደበኛ ስራዎች በቴክኖሎጂ አውታሮች መታገዛቸው ለተገኘው አዎንታዊ ውጤት ገንቢ ሚና ተጫውቷል ብለዋል::

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ፥ በፌዴራል የገቢዎች ሚንስቴር ሀዋሳ ቅርንጫፍ የ2017 በጀት አመት እቅድ 6 ነጥብ 13 ቢሊዮን ብር የመንግሥት ገቢ የመሰብሰብ ቢሆንም፥ እቅዱ ከዚህ ቀደም ከነበረው እጥፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በግማሽ አመቱ 2 ነጥብ 42 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዘን ወደ ስራ ገብተናል ያሉት አቶ ሀብታሙ የዕቅዱን 95 በመቶ ማሳካት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

ቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ የሲዳማ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ እና በከፊል ኦሮሚያ ክልል አገልግሎት እየሰጠ ያለው ያለ ሲሆን ዋናው ቅርንጫፍ ጨምሮ ንዑስ ቅርንጫፎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር እንዲሁም የደንበኞችን ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ኦን ላይን በማድረግ የሀብትና የጊዜ ብክነት ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል።

የግብር ከፋዩን ህብረተሰብ ንቃት ለማሳደግ ሰፊ ትምህርት እና ስልጠና በተለያዩ አማራጮች እየተሰጠ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ፥ ግብርን በራስ ፍላጎት የመክፈል ባህል እያደገ መጥቷል ብለዋል። ነገር ግን አሁንም ጠንካራ ስራ ይፈልጋል ነው ያሉት።

የግብር ከፋዮችን ቅሬታና አቤቱታ የሚሰማ የስራ ክፍል ያለ ሲሆን በግብር ከፋዮች ለሚነሱ ቅሬታዎች በህግ አግባብ ምላሽ በመስጠት የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ መ/ቤቱ እየሰራ ነው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ ደረሰኞችን ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን ወደ ሰራ ሲገባም ከደረሰኝ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን የግብር ማጭበርበር በእጅጉ ለመቀነስ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል አቶ ሀብታሙ ታደሰ።

ዘጋቢ: ጀማል የሱፍ