ኤጀንሲው ከተቋቋመለት ዓላማ እና ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ገለጸ

ኤጀንሲው ከተቋቋመለት ዓላማ እና ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ገለጸ

ኤጀንሲው የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ከዞን ህብረት ሥራ ልማት ማህበር ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በይርጋ ጨፌ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አፀደ አይዛ፤ የክልሉን ዜጎች በመጥቀም ላይ የሚገኙ በ6 ሺህ 2 መቶ 84 መሰረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት አማካይነት 4 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ሀብት እንዲሁም 1 ነጥብ .5 ቢሊዮን ብር የተጣራ ካፒታል እና ከ8 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ቁጠባ በማሰባሰብ ውጤታማ ሥራ የሚሠሩ ህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው ለአባላት እና ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አክለውም የህብረት ሥራ ማህበራት ዋነኛው ትኩረታቸው በገጠር እና በከተማ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሰረታዊ ችግሮችን በመፍታት የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በመሆኑ በተለይም አምራች እና ሸማቾችን በማስተሳሰር የከተማውን እና የገጠሩን ኢኮኖሚ ትስስሩ ጤናማ፣ የተቀናጀ እና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን በትኩረት እየተሠራ መሆኑን በመጠቆም ኤጀንሲው ከተቋቋመለት ዓላማ እና ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ የልማት ዕቅድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል አታራ፤ ተቋሙ በክልሉ በ12ቱም ዞኖች የሚገኙ ህብረት ሥራ ማህበራትን ድጋፍ እና ክትትል ከማድረግ ባሻገር የሪፎርም ሥራ መሠራቱን በመጠቆም በተለይ ባለፉት 6 ወራት አዳዲስ አባላትን ለማፍራት በተሰራው ሥራ በ2016 በጀት ዓመት ከነበረው 9 መቶ 81 ሺህ አባላት ተጨማሪ አባላትን በማፍራት አጠቃላይ 1 ሚሊዮን 50 ሺህ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይ በጉድለት የታዩ ችግሮችን በተመለከተ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በብድር የሚሰራጨውን የአፈር ማዳበሪያ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ከማስመለስ አንጻር የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል።

በመድረኩ የኤጀንሲው የ6 ወር አፈጻጸም ሪፖርት እና የመስክ ምልከታ ግብረ መልስ ተሰጥቶ ውይይት ተደረጎበታል።

በውይይት መድረክ የተገኙ የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በጥንካሬ የተነሱ ጉዳዮችን በማስቀጠል ጉድለቶችን በቀጣይ ለማረም በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን