በቤንች ሸኮ ዞን የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ በይፋ ተጀመረ
ሀዋሳ፡ ጥር 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቤንች ሸኮ ዞን የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ በሼይ ቤንች ወረዳ ማዝ ቀበሌ በይፋ ተጀምሯል።
በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች የተፈሰስ ልማት ስራው በይፋ የተጀመረ ሲሆን በቤንች ሸኮ ዞን ሼይ ቤንች ወረዳ ማዝ ቀበሌ የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም የክልልና የዞን አመራሮች በተገኙበት የተፋሰስ ልማት ስራ ተከናውኗል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሃላፊው አቶ መስፍን መንገሻ እንደተናገሩት፤ የአፈር ሀብታችንን መጠበቅ ተፈጥሮን መንከባከብና የውሀ ሀብታችንን መጠበቅ በመሆኑ ዘንድሮ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው።
የተፋሰስ ልማት ለበርካታ አመታት እየተሰራ የቆየና በህዝቡ ውስጥ ባህል ሆኖ የቆየ ተግባር መሆኑን ገልጸው፤ ዘንድሮ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ የመኖ ሳርና መሰል ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል።
የዞኑ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ እንደተናገሩት፤ በዞኑ በ96 ንዑስ ተፋሰሶች 34ሺ 480 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ይሰራል።
የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራችንን መስራት የአፈር ለምነትን በማስጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።
በስራው የተሳተፉ አርሶ አደሮችም የተፋሰስ ልማቱ ለምርታማነት ዕድገት ከሚኖረው አስተዋጽኦ በተጨማሪ የመሬት መንሸራተትን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል
በዞኑ ለ45 ቀናት በሚቆየው የአካባቢ ጥበቃ ስራ 34ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን 96 ተፋሰሶች ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ተለይተዋል።
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ