ለህዝቦች አንድነትና ልማት የሚያገለግሉ ዕሴቶችን መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባ በሀድያ ብሔር የሸምበለላ አበጋዞች ማህበር አስታወቀ
ማህበሩ በሀድያ ዞን ጎምቦራ ወረዳ ማልዶ ቀበሌ የደደች መለሰ ሀንቅሶ ከብቶችን መቶ የማስቆጠር የ”ወገና” ስነ-ስርዓት አካሂዷል።
ደደች መለሰ ሀንቅሶ በሀድያ ዞን ጎምቦራ ወረዳ ማልዶ ቀበሌ ለ17 ዓመታት ስራው የሚጠይቀውን የተለያዩ ተግዳሮቶችን በድል ተወጥተው ያረቡትን ከ1መቶ በላይ ከብቶችን በማስቆጠር በ”ወገና” ስርዓት ከብቶችን አስመርቀዋል።
በዚህ ስነ-ስርዓት ላይ ከተሳተፉት አበጋዞች መካከል የቀድሞ የሸምበለላ አበጋዞች ማህበር አስተባባሪ አበጋዝ ዓለሙ ቀልባሞ እና የማህበሩ አባል ደደች ፀጋዬ ሰብሮ፤ የ”ወገና” ስርዓት ከብቶችን የማስቆጠርና የማስመረቅ ተግባር ብቻም ሳይሆን በሕዝቦች መካካል አንድነትና ልማትን የማስቀጠል መልካም ዕሴት ነው ብለዋል።
ከብቶችን መቶ እና እስከ ሺህ በማስቆጠር ምርቃቱን የሚፈልግ አንድ የከብት አርቢ አስቀድሞ ለአበጋዞች ማህበር በማሳወቅና ዕውቅና ሲያገኝ ብቻ ማስመረቅ እንደሚችል የተናገሩት ባላማዕረጎቹ በ”ወገና” ስርዓት ከብቶችን ወንዝ የማሻገር ትርጉሙም ሀብቱና መልካም ዝናው ለቀጣይ ትውልድ እንዲሻገር በመመኘት እንደሆነም ገልፀዋል።
ሌላኛው በዚህ ስነ-ስርዓት በባህሉ መሠረት “ሀንጩፋ” የማሰር ስነ-ስርዓት ሲሆን ትርጉሙም ከዚያች ዕለት ጀምሮ አንድ ከብት አስቆጣሪ የእሱም የባለቤቱም ቀድሞ የነበራቸው መጠሪያ በማዕረግ ስም እንደተቀየረላቸው ማሳያ እንደሆነና ለዚህም ማድረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄ ጭምር የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ሻምበል ፀጋዬ ሀንቅሶ እና ወ/ሮ አበባ ሀንቂሶ የደዳች መለሳ ወንድምና እህት ሲሆኑ እንደ ቤተሰብ ወንድማቸው ለዚህ ክብር በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ የነበሩት ተግዳሮቶች እጅግ ተስፋ አስቆራጭ እንደነበረም አስታውሰዋል።
ገና የአንድ ወር ሙሽራና የመቶ ከብቶች አስቆጣሪ የሆኑት ደዳች መለሰ ሀንቅሶ በበኩላቸው፤ አባታቸው በ1992 ዓ.ም ከብቶቻቸውን መቶ ካስቆጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ከብት በመጠበቅ ራሳቸውን ሲያዘጋጁ እንደነበር በማስተወስ እርሳቸውም እርባታውን ሲጀምሩ ለከብቶቻቸው ሳር ፍለጋ ከዞኑ ወጪ በርካታ አካባቢዎችን እንደተዘዋወሩ ተናግረዋል።
ደዳች መለሰ በትምህርታቸው ባገኙት ውጤት ዩኒቨርሲቲ የመግባት ፍላጎት ቢኖራቸውም አባታቸው ደዳች ሀንቅሶ የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ ባዘዙት መሠረት ወደ ከብት እርባታ መግባታቸውን የሚናገሩት ደዳች መለሰ እርሳቸውም ለልጅ የማስተላለፍና እስከ አንድ ሺህ ከብቶችን የማስቆጠር ህልም እንዳላቸውም አክለዋል።
ስርዓቱን አስመልክቶ አስተያየት የሰጡት የጎምቦራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ጎበና የወገና ስርዓት አንዱ የሀድያ ብሔር ጠንካራ የስራ ትጋትን የሚያሳይ እንደሆነ በመግለፅ ይህንን መልካም ዕሴት ለትውልድ ለማስተላለፍ ህብረተሰብና መንግስት በልዩ ትኩረት መስራትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የስርዓቱ ባለቤቶች የሆኑ አበጋዞችም ለአካባቢያቸው ብሎም ለሀገር የሚጠቅሙ መልካም ዕሴቶችን ወደፊት በማምጣት የበኩላቸውን እንድወጡም ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የተመዘገቡ አበረታች ዉጤቶችን በቀጣይ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ
በዳዉሮ ዞን በዘንድሮ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት 40 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የዞኑ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ ልማት መምሪያ አስታወቀ
በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ተግባራት የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የጃጁራ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ተናገሩ