በዞኑ አበሽጌ ወረዳ በትምህርት፣ በጤናና በሴቶች ተጠቃሚነት ላይ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ላይ ይበልጥ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ገለፀ

በዞኑ አበሽጌ ወረዳ በትምህርት፣ በጤናና በሴቶች ተጠቃሚነት ላይ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ላይ ይበልጥ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ገለፀ

የዞኑ ምክር ቤት የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በወረዳው የተለያዩ ስራዎችን ምልከታ አድርጓል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የሴቶች እና ማህበራዊ፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም የህግ፣ ፍትህ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በተለያዩ ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች የተከናወኑ ተግባራት እና ያጋጠሙ ችግሮች እና በቀጣይ መሰራት በሚገባቸው ስራዎች ዙሪያ ምልከታ በማድረግ ላይ ናቸው።

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኪሚቴ በአበሽጌ ወረዳ በ1969 ዓ.ም የተመሰረተው የቱሉላሜ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የቱሉላሜና ተሊሎ ጠቅላላ ጤና ኬላ ግንባታ፣ በቱባና ተሊሎ በጥምር ግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች ልማትና በወረዳው ማእከልም በየሴክተር መስሪያ ቤቶች እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የአካል ምልከታ በማድረግ የጋራ ውይይት ተደርጓል።

592 ተማሪዎችን ከቅደመ መደበኛ አስከ 8ኛ ክፍል የሚያስተምረው የቱሉላሜ ሙሉ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሉበት ችግሮች ለመፍታት ጥረት ማድረጉ የሚበረታታ ቢሆንም የትምህርት ግብአት በማሟላት የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ጥሩነሽ ምኑታ ጠቁመዋል።

የወንበር ጥምርታ፣ የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት፣ የፈተና አሰጣጥ ስርዓት እና የጉራጊኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት በጥሩ ሁኔታ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ለላቼ፣ ለአቡኮ፣ ለቱልላሜ እና ለቱባና ተሊሎ ታሳቢ ተደርጎ ህብረተሰቡ እና መንግሥት በጋራ ሆነው በ15 ሚሊዮን ብር የተጀመረው ጠቅላላ ጤና ኬላ ግንባታ ሲጠናቀቅ የብዙሀኑ ችግር እደሚፈታ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የዞኑ ምክር ቤት የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ አስቴር ግዛው በቱባና ተሊሎ በፍየል እርባታ በእርሻ ስራ እንዲሁም በቁጠባ እና ብድር የተደራጁ ሴቶች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ሙያዊ ድጋፍ እና የአፈር ማዳበሪያ እንዲሁም የምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ የገጠማቸው ችግር ሊፈታ ይገባል ብለዋል። የገበያ ትስስር በመፍጠር በኩልም ትኩረት ያሻል ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ምልከታ ባደረገባቸው አካባቢዎች የነበሩ ባለድርሻ አካላት ስራዎቻቸውን መታየቱ እንዳስደሰታቸው እና ጠንካራ ጎኖች አጎልብቶ በማስቀጠል ክፍተቶችን ለማረም ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል።

የአበሽጌ ወረዳ ትምህርት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ እንግዳ ጥሩሃ፤ በወረዳው በሚገኙ 44 ትምህርት ቤቶች 19 ሺህ 693 ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ መሆናቸውን በመግለፅ 82 የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት መማሪያ ጣቢያዎች ቢኖሩም በ23ቱ ጣቢያዎች ብቻ በትክክል ይማራሉ ብለዋል።

የጉራጊኛ፣ የሂሳብ እና የእንግሊዝኛ ትምህርት መምህራን እጥረት በወረዳው በብዙ ትምህርት ቤቶች መስተዋሉን በመግለፅ ክፍተቱን ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግርዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የትምህርት ግብአት ለማሟላት እና የመማሪያ አካባቢዎች ምቹ ለማድረግ መንግስት፣ ህብረተሰቡ እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በማሳተፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታው ወቅት በታዩ ጠንካራ እና መስተካከል ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከወረዳው ምክር ቤት፣ ከጤና እና ከሴቶች እና ህፃናት ጽ/ቤት ሀላፊዎች እንዲሁም ማናጅመንት እና ከሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ጋር የጋራ ውይይት ተደርጓል።

ዘጋቢ፡ እንዳልካቸው ደሳለኝ – ከወልቂጤ ጣቢያችን