በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ 4ሺህ 750 ሄክታር መሬት በስነ-አካላዊና በስነ-ህይወታዊ ስራ ለመሸፈን መታቀዱን በስልጤ ዞን የሳንኩራ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ

በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ 4ሺህ 750 ሄክታር መሬት በስነ-አካላዊና በስነ-ህይወታዊ ስራ ለመሸፈን መታቀዱን በስልጤ ዞን የሳንኩራ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ

በወረዳው “የተፋሰስ ልማት ስራችን ለብልፅግናችን” በሚል መሪ ቃል የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ወረዳዊ የመክፈቻ ፕሮግራም በበርጮ ቀበሌ ተካሂዷል።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ ሙለጌ ሙዴ እንደገለፁት፤ ባለፉት አመታት እንደ ሀገር የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ስራ ዉጤት የታየበት ነዉ።

የዘርፉን ሁለንተናዊ ውጤታማነት በማሳደግ ሀገራዊ ልማትና ብልፅግና በማረጋገጥ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን በማንሳት በወረዳ ደረጃም ባለፉት ተከታታይ አምስት አመታት በህዝብ ንቅናቄ በተደራጀ የልማት ሰራዊት ሰፊ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች በተሳካ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የተፋሰስ ልማት ስራው በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ለመገንባት ብሎም ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

ለዚህም ማሳያው በወረዳው ባገገሙ መሬቶች ላይ ስራ አጥ ወጣቶች በመደራጀት በመስኖ፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በድለባ ዘርፎች በርካቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዘንድሮውን የተፋሰስ ልማት ስራ በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ሲሉ ዋና አስተዳዳሪዋ ወ/ሮ ሙለጌ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሳንኩራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙሀባ ሳሊያ በበኩላቸው፤ የተፋሰስ ልማት ስራው በተጠናከረ ሁኔታ መተግበሩ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሰው ማገገም እንዲችሉ፣ የከርሰ-ምድርና ገፀ-ምድር ውሃ እንዲጨምር ብሎም ምርትና ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ እንዲችል ያደረገ ሲሆን ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚነትም የላቀ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል።

በወረዳው በበርጮ ቀበሌ “የተፋሰስ ልማት ስራችን ለብልፅግናችን” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ነባር ተፋሰሶችን የመጠገን፣ ለበጋ መስኖ የሚውል የውሃ ማሰባሰብ ስራ፣ ለምርትና ምርታማነት ዕድገት የሚረዱ የተጎዱ መሬቶችን መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አመላክተዋል።

በአጠቃላይ በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ 32 ሺህ 5መቶ 86 የሰው ኃይል በማሳተፍ 4ሺህ 750 ሄክታር መሬት በተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የሚለሙ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርታማነትን በማሳደግ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረ ወዲህ የዘርፉን ውጤታማነት በተጨባጭ ማየት ከመቻልም በላይ በግብርናው ዘርፍ ለተመዘገበው ውጤትና ዕድገት መረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ለተፈፃሚነቱ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አቶ ሙሀባ ተናግረዋል።

በበርጮ ቀበሌ በተጀመረው ወረዳዊ የተፋሰስ ልማት ስራ ንቅናቄው ላይ የተገኙት አርሶ አደር አቶ በድሩ ሙጎሮ፣ አክመል ሳሊያ እና ወ/ሮ ሽቱ አብዶ፤ ባለፉት አመታት የተከናወኑ የተፈጥሮ ልማት ስራዎች ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ የነበራቸውን ጉልህ ድርሻ በማሳቸው ማየት መቻላቸውን በማንሳት በዚህ ዓመት የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት እንዲቻል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ሃጀራ ግርማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን