የተጎዳ መሬትን መልሶ ለማልማት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ አርሶአደሮች ተናገሩ
ባህር ዛፍ የመሬትን ለምነት እየቀነሰ በመሆኑ ተክሉን በተፋሰስ ልማት ሥራ ከአርሶአደሩ ማሳ በዘመቻ የማስወገድ ተግባር መጀመሩን የወረዳው ግብርና ልማት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
በጎርፍና በሌሎች ምክንያቶች የተጎዱ መሬቶችን መልሶ በማልማት የተገኙ ውጤቶችን በማየት የተፋሰስ ልማት ሥራ ተግባር በማሳቸው መጀመራቸውን የወረዳው አርሶ አደሮች ዓለሙ ጅግሶና በቀለ በየነ ገልፀዋል፡፡
ለአንድ ወር ቆይታ በዘመቻ በሚካሄደው በተፋሰስ ሥራ የተጎዳ መሬትን መልሶ ለማልማት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አርሶአደሮቹ ተናግረዋል፡፡
በወረዳው ዱመርሶ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተሻለ ከፍያለው እንደገለፁት፤ በቀበሌያቸው በአንዳንድ አካባቢዎች በባህር ዛፍ ተክል የተሸፈኑ መሬቶች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ሰብሎች ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ ለአርሶአደሩ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት በዘመቻ ባህር ዛፍን በመንቀል በቦታው አርሶአደሩ ቡናና እንሰት እንዲተክል በማቀድ የእርሻ ቅድመ ዝግጅት መጀመራቸውን አቶ ተሻለ አስረድተዋል፡፡
የይርጋጨፌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ጅግሶ እንደገለፁት፤ በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱ መሬቶችን ለይቶ በማቀድ የ2017 ዓ.ም የተፋሰስ ልማት ሥራ ጥር 15 በዘመቻ ተጀምሯል፡፡
የአፈርና ዉሃ ጥበቃ ሥራ፣ የቡና ጉድጓድ ዝግጅት፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (የኮምፖስት) ዝግጅት፣ ተዳፋታማ የእርሻ ቦታዎችን እርከን የማዘጋጀት ሥራ በተፋሰስ ልማት ከሚከናወኑት ተግባራት የሚጠቀስ መሆኑን የተናገሩት አቶ ክፍሌ፤ የባህር ዛፉ የመሬትን ለምነት ስለሚቀንስ ተክሉን አርሶአደሩ ከማሳው እንዲያስወግድ በዘመቻ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሳውላ ካምፓስ ለ9ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 121 ተማሪዎችን አስመረቀ
ዲግሪው “ወረቀት ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ተስፋና የትውልድ ኃላፊነት ነው” – አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር)
በክልሉ የተጀመሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድጋፍና ክትትል ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ