በትምህርት ቤቱ የተሻለ የመማር ማስተማር ሥራ ቢኖርም መሟላት ያለባቸው የግብዓት ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባ በቤንች ሸኮ ዞን ባለ ልዩ ተሰጥኦ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገለፁ
ሀዋሳ፡ ጥር 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በትምህርት ቤቱ የተሻለ የመማር ማስተማር ሥራ ቢኖርም መሟላት ያለባቸው ግብዓትና መሰል ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባ በቤንች ሸኮ ዞን ባለ ልዩ ተሰጥኦ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገልጸዋል።
የቤንች ማጂ ልማት ማህበር በበኩሉ ተማሪዎች ያቀረቧቸው ዕጥረቶች እንዳሉ በመጠቆም ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክቷል።
የቤንች ማጂ ልማት ማህበር ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ከወረዳና ከተማ አስተዳደሮች የተመለመሉ ልዩ ተስጥኦ ያላቸው ተማሪዎችን በመቀበል በአዳሪ ትምህርት ቤት እያስተማረ ይገኛል።
ካነጋገርናቸው ባለ ልዩ ተስጥኦ አዳሪ ት/ቤት ተማሪዎች መካከል ከ9ኛ ክፍል ተማሪ አማኑኤል አድማሱ፣ ከ10ኛ ክፍል ተማሪ ፍቅረተ ጃሹ እና ተማሪ ስጦታ ግርማ ከ11ኛ ክፍል በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም ከነበሩበት ወደ አዳሪ ት/ቤት በመምጣታቸው የተሻለ የመማር ማስተማር ዕድልን እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ አክለውም ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን የምግብ የህክምናና የላብራቶሪ ግብኣት ዕጥረቶች እንዲቀረፉላቸው ጠይቀዋል።
በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የሚገኘው የሚዛን ዕድገት ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መደበኛውን ጨምሮ የባለ ልዩ ተስጥኦ አዳሪ ት/ቤት ተማሪዎችን አካቶ ከ900 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ይዞ ከመስራትም ባለፈ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ርዕሰ መምህሩ ዝናው ታደሰ ገልፀዋል።
የባለ ልዩ ተስጥኦ ተማሪዎች ት/ቤት አስተባባሪ መምህር መኳንንት በየነ በበኩላቸው፤ ተማሪዎች የተሻለ ዕውቀት እንዲያገኙና በስነ-ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የቤንች ማጂ ልማት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አፀናኝ ፈለቀ እንደገለፁት፤ የልማት ማህበሩ እያስተዳደረ የሚገኘው የባለ ልዩ ተስጥኦ ተማሪዎች ት/ቤት የተሻለ ቦታ ለማደረስ በየወሩ ከ45 ሺህ ብር በላይ ወጪን በማውጣት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እየሰራ ይገኛል።
ማህበሩ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የምግብና የመኝታ አገልግሎት በመስጠትና የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ደግሞ የመምህራንን ጥቅማ ጥቅም በመሸፈን ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ የሚስተዋሉ የግብኣት ችግሮች የምግብና የህክምና ዕጥረቶችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አቶ አፅናኝ አብራርተዋል።
በተለይም በ2018 የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች በኦን ላይን ፈተና የመውሰድ ልምድን እንዲያጠናከሩ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ በቀጣይ ውጤታማ ዜጋን ከማፍራት አኳያ ወላጆችና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ በማደረግ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዘበዋል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/