ዜጎች የህክምና አገልግሎት በህመማቸው ልክ እንጂ በኪሳቸው መጠን እንዳይሆን የማህበረሰብ ጤና መድህን ያለው አስተዋዕፆ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ

ዜጎች የህክምና አገልግሎት በህመማቸው ልክ እንጂ በኪሳቸው መጠን እንዳይሆን የማህበረሰብ ጤና መድህን ያለው አስተዋዕፆ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ጥር 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ዜጎች የሚያጋጥማቸውን የጤና እክል በመክፈል አቅም እጦት ምክንያት፥ የህክምና አገልግሎት ሳያገኙ እንዳይቀሩ ለማስቻል በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በኩል ዘላቂ የሆነ ማህበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በርካታ ቁጥር ያለው የክልሉ ህዝብ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ መሆን በመቻላቸው ከሃሳብና ጭንቀት ተገላግለው እፎይታ ማግኘታቸውን ነው በሰጡት አስተያየት የገለጹት።

በስልጤ ዞን ቂልጡ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ረሂማ ከድር ሁሴን በዕድሜ ማምሻ በገጠማቸው የከፋ የጤና መታወክ አልጋ ላይ ከዋሉ ሰንበትበት ብለዋል። አቅም ፈቅዶ መታከም የሚያስችል ገንዘብ በማጣታቸው ከህመማቸው ጋር የአልጋ ቁራኛ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

አብሮ ለከረመ ህመማቸው መድህን ፍለጋ የሰዉ እጅ ማየት ግድ ቢላቸው ጠይቆ ከማፈር በስተቀር መፍትሔ አልሆናቸውም። ይልቁንም ከጎረቤታቸው አንደበት የሰሙት ንግግር አንዳች የምስራች ያዘለ፥ ከህመማቸው በዘላቂነት መታከም የሚያስችል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መኖሩን አስረዳቸው። ለዚህም ጊዜ ሳይወስዱ ፈጥነው በመመዝገብ መልካም ዕድል ይዞላቸው የመጣውን የጤና መድህን መቀላቀላቸውን ይገልጻሉ፡፡

ወ/ሮ ረሂማ እንደሚናገሩት በጤና መድህን አገልግሎት አማካኝነት ከጤና ጣቢያ እስከ ሆስፒታል ሄደው መታከም ችለዋል፡፡ የጤና ክትትልም ሆነ ህክምና ማድረግ የጀመሩት ደግሞ የጤና መድህን አባል ከሆኑ በኋላ ቢሆንም፥ ይህን አገልግሎት ብዙ ጊዜ ሲያሰቃያቸው የነበረውን የአስም፣ የሳንባና ከግፊት በሽታ ታክመው በመዳናቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል። ህክምናቸውን ጨርሰውና ከህመማቸው አገግመው እስኪወጡ ድረስ ምንም አይነት ወጪ ሳያወጡ አልጋና መድሀኒትን ጨምሮ ለህክምና የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን ከሆስፒታሉ አግኝተው መታከም ችለዋል፡፡

በወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ሆስፒታል በህፃናት ህክምና ውስጥ ልጇን ስታስታምም ያገኘናት ሌላኛዋ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ የላንፍሮ ወረዳ ግራር ጦራ ቀበሌ ነዋሪ ዘኪያ ኤገኖ ናት። በደከመ የዕንባ ሲቃ ታጅባ በሰጠችው አስተያየት፥ “ዛሬ ማህረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ባይኖር ኖሮ ሌጄን ቀብሪያት እኔም ሞቼ ነበር ትላለች።” ሰው በህመሙ ልክ ድጋፍና ህክምና ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ በዚህ ልክ መኖሩ እፎይታ እንደሰጣት ትናገራለች።

እናቷን የሳንባ ምች እና ካንሰር እያስታመመች ያገኘናት ሀድራ ሱልጣን በበኩሏ፥ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የእናታችንን ህይወት ከመታደጉም በላይ ገንዘብ ከኪሳችን አውጥተን ማሳከም እንችልም ትላለች። “ይህ እድል ባይኖር ኖሮ እናቴ ከህመሟ ጋር እየተሰቃየች ወይም ደግሞ እስካሁን ሞታ ይሆን ነበር በማለት ትናገራለች።

በአመት አንድ ጊዜ ከ800 እስከ 1ሺህ ብር በሚሆን መዋጮ የተለያየ የጤና አገልግሎት በተለያየ ጊዜ እንዲያገኙ መንግስት እየሰራ ነው ያሉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ናቸው።

በ2016 ዓ.ም በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

የጤና ተቋማት አገልግሎትን በማሻሻል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባላት የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግና ተጨማሪ አዳዲስ አባላትን በማፍራት ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የማዕከላዊ ኢተዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው፥ ማንም ሰዉ ህክምና ማግኘት ያለበት በህመሙ ልክ እንጂ በኪሱ መጠን መሆን የለበትም ይላሉ። የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የክልሉን ህዝብ የጤና አገልግሎት ፍትሃዊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚያከናውናቸዉ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን አመላክተዋል።

መሪው ብልጽግና ፓርቲና መንግስት ለዘርፉ በሰጡት ትኩረት ባለፉት ዓመታት በርካታ የክልሉን ነዋሪዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ብለዋል። ከዚህ አንጻር በ2016 ዓ.ም ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ ዜጎች የጤና መድህን አባል ሆነው ከመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ከአጠቃላይ የክልሉ ህዝብ 78 በመቶ የማህበረሰብ አቀፍ ጠየና መድህን ተጠቃሚ መሆኑን ጠቁመው በዘንድሮ በጀት አመት 90 በመቶ ለማድረስ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ