”የመሬት ሀብታችን ለብልፅግናችን” በሚል መሪ ቃል የ2017 ዓ.ም የተፋሰስ ልማት ስራ በደምባ ጎፋ ወረዳ ቦርዳ ቀበሌ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ የተገኙት የጎፋ ዞን ሴቶችና ህፃናት መምሪያ ኃላፊና የወረዳው ተፋሰስ ልማት አስተባባሪ ወይዘሮ ፀጋነሽ እንግዳ፤ ዘንድሮ የተፋሰስ ስራዎች ”የመሬት ሀብታችን ለብልጽግናችን” በሚል መሪ ቃል በሀገር ደረጃ ተጀምሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረው ስራው አካባቢያችንን ለመጠበቅ፣ ከጎርፍ አደጋዎች ለመታደግ፣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና ለአፈር ሀብታችን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
የአንድ ሀገር ልማትና ብልጽግና ያለ ሴቶች ተሳትፎ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ተናግረው፤ አካባቢ ሲራቆትና ሲጎዳ ይበልጥ ተጎጂዎች ሴቶችና ህፃናት ስለሆኑ ሴቶች በስፋት እየተሳተፉ መሆናቸውን አንስተዋል።
የደምባ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳደር አቶ አንዳርጌ አራታ የተፋሰስ ስራ አፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመሆኑ የሁሉም ሰው ስራ መሆን እንዳለበት አሳስበው የመንግስትም ይሁን የግል ደኖች ተመንጥረው በማለቃቸው መሬት ምርትን በአግባቡ እንዳይሰጥ እያደረገ ነው ብለዋል።
የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ አቶ አድማሱ አላ እና ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ሊበና በወረዳው ባሉት በ34 ቀበሌያት 10 ሺህ 334 ሄክታር መሬት በተፋሰስ የሚለማ ሲሆን ከእነዚህ በዋና ዋና ስትራክቸር 4 ሺህ 134 ሄክታር መሬት እንደሚለማ ተናግረዋል።
በዚህም 40 ሺህ 853 ሰዎች እንደሚሳተፉ ጠቁመው በቀጣይ 30 ቀናት በትኩረት እንደሚሰራም አንስተዋል።
የቀበሌው ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክንፈ ጋርቦ በቀበሌው ባሉት ሶስት ዋና ዋና ተፋሰሶች 842 ሄክታር መሬት የሚሸፍን መሆኑን ተናግረው አሁን በ278 ነጥብ 34 ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረ ሲሆን ቦታው ለጎርፍ ተጋላጭ መሆኑን አስረድተዋል።
ከእነዚህ በአርሶ አደር 64 ሄክታር፣ በሴቶች 29 ሄክታር እና ወጣቶች 27 ሄክታር መሬት እንደሚለማ ተናግረው 1ሺህ 58 ሰዎች ሲሳተፉ በገንዘብ ሲተመን ከ3 ሚሊዮን 132 ሺህ ብር በላይ መሆኑን አብራርተዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል አርሶአደር ጋሻው ገዛኸኝ፣ ወጣት ካለብ ተስፋዬ እና በቀበሌው የሴቶች ተወካይ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ኩሳ በጋራ እንደተናገሩት፤ ከዚህ በፊት አካባቢው የተሻለ አየር ፀባይ ቢኖርም በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ደንና የግለሰቦች ማሳ መራቆቱን አንስተው ዘንድሮ ጥቅሙ የኛ መሆኑን ተረድተን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለ30 ቀናት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የሐይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች በቦታው ተገኝተው በፀሎትና በምርቃት አስጀምረዋል።
ዘጋቢ፡ ኢያሱ አዲሱ – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/