የጌዴኦ ብሔር የዘመን መለወጫ ዳራሮ በዓል በዞኑ ራጴ ወረዳ ድቤቲ ሶንጎ በአባገዳው ፀሎትና ሌሎች ባህላዊ ኩነቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡
የአንድን ማህበረሰብ ልማድ እንዲሁም ታሪክ ማስተላለፊያና የሕይወት መልኮችን መግለጫ አንዱ ሰበዝ የሆነው ኪነ-ጥበብ የብሔሩ የዘመን መለወጫ ዳራሮ በዓል መከበር ከጀመረበት ጥር አንድ ጀምሮ በዓሉን እያደመቀ ይገኛል።
ከማድመቂያነቱና ህዝቡን ከማዝናናቱ ባለፈ ደግሞ በቀደምት አባቶች ተጠብቆ የቆየውን የብሔሩን ባህላዊ እሴቶችን ለቀጣይ ትውልድ ከማሸጋገር አኳያ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ያነጋገርናቸው የዘርፉ ባለሙያዎችና የበዓሉ ታዳሚዎች ተናግረዋል፡፡
ድምጻዊ መላኩ ሽፈራው እና የአከባቢው ነዋሪና ባህል አዋቂ አቶ በቀለ ሂጆ ኪነ ጥበብ የአንድን አከባቢ ሁለንተናዊ ዕድገት ከማረጋገጥ አኳያ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ በዞኑ የባህል ማዕከል በመገንባት ያለውን ሀብት ወደ አንድ ማዕከል ለመሰብሰብና ዘርፉን በዕውቀት ለመደገፍ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የአንድን ማህበረሰብ የአኗኗር፣ የሥራ ባህል፣ የቋንቋ፣ የባህላዊ አስተዳደር ሥርዓትና ሌሎች ባህላዊ እሴቶችን ከማሳደግና ለዓለም ከማስተዋወቅ አኳያ ኪነጥበብ የማይተካ ሚና እንዳለው የራጴ ወረዳ ባህል ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ከበደ ገልፀው በአከባቢው ያሉ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን በማልማት ለአለም ለማስተዋወቅ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣው የብሔሩ ባህል፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ወግ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ኪነጥበብ ያለውን ሚና በመገንዘብ መንግስት ፣ ባለሀብቱና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ የራጴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ሂኔሲ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ሳሙኤል በቀለ ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/